Ethiopia - Collective Agreements Database



በዕድገት ድርና ማግ የስፌት ክር አክስዮን ማህበር


እና


በዕድገት ድርና ማግ የስፌት ክር አክስዮን ማህበር መሠረታዊ ሠራተኛ ማኅበር


መካከል


ለ15ኛ ጊዜ የተደረገ የሕብረት ስምምነት




አዲስ አበባ 

ግንቦት 200ዓ.ም 

ክፍል አንድ

የህብረት ስምምነቱ ዓላማና አስፈላጊነት፣ የቃላት አተረጓጎም፣ እውቅና እና 

የህብረት ስምምነት ተፈፃሚነት ወሰን

አንቀጽ 1

የህብረት ስምምነት ዓላማና አስፈላጊነት

የህብረት ስምምነት ዓላማና አስፈላጊነት የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 እና የዚህ አዋጅ ማሻሻያ 494/98 እንደተጠበቀ ሆኖ በተጨማሪ አዋጁ ለህብረት ስምምነት የተዋቸውን መብቶችና ሌሎችንም በዚህ ህ/ስምምነት ውስጥ ስምምነት የተደረሰባቸውን ጉዳዮች በድርጅቱ ውስጥ በአሰሪና ሰራተኛ መካከል ያለው የሥራ ግንኙነት ጤናማ እንዲሆን እና አሠሪና ሠራተኛውም መብትና ግዴታውን አውቀው በአንድነት ለጋራ ጥቅም ለድርጅቱ ህልውና እና ለሠራተኛ መብት መጠበቅና ለኢንዱስትሪ ሰላም መስፈን ተጣጥመው እንዲሰሩ ለማድረግ ነው፡፡ 

አንቀጽ 2

የመሪ ቃሎች ትርጉም

በዚህ ህብረት ስምምነት የመሪ ቃሎች ትርጉም ከዚህ በታች የተሰጠው ትርጉም ይኖረዋል፡፡ 

2.1. ፋብሪካ፡- ማለት ዕድገት ድርና ማግ የስፌት ክር አክስዮን ማህበር ማለት ነው፡፡ 

2.2. የሠራተኛ ማህበር፡- ማለት የዕድገት ድርና ማግ የስፌት ክር አክስዮን ማህበር መሠረታዊ ሠራተኛ ማህበር ማለት ነው፡፡  

2.3. የደረጃ ዕድገት፡- ማለት በድርጅቱ መዋቅርና በአስተዳደር የሥራ መመሪያ መሠረት ከዝቅተኛ የሥራ መደብ ወደ ቀጣዩ ወይም ወደ ከፍተኛ የሥራ መደብ የሚደረግ የሥራ ምደባ ነው፡፡ 

2.4. ሠራተኛ፡- ማለት በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ 377/96 አንቀጽ 2 ንዑስ አንቀጽ 3 መሠረት የተሰጠው ትርጉም ይኖረዋል፡፡ 

2.5. አሰሪ፡- ማለት በአሰሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 2 ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት የተሰጠው ትርጉም ይኖረዋል፡፡ 

2.6. የሥራ መሪ፡- ማለት በአሰሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 እና ተሻሽሎ በወጣው አዋጅ ቁጥር 494/98 የተሠጠው ትርጉም ይኖረዋል፡፡ 

2.7. ውክልና፡- ማለት አንድ የስራ መሪ ከአለው የሥራ ኃላፊነት ላይ በተጨማሪ የተጓደለ የኃላፊነት ሥራ ቦታን ደርቦ እንዲሠራ ወደ ላይ የሚሰጥ ኃላፊነት ነው፡፡ 

2.8. የውጤት ክፍያ፡- ማለት አንድ ሠራተኛ በውጤት በሚከፈል የማምረቻ መሣሪያ ላይ ሲሰራ ብቻ በፋብሪካው የውጤት ክፍያ መመሪያ መሠረት የሚከፈል ክፍያ ማለት ነው፡፡ 

2.9. የማትጊያ ክፍያ፡- ማለት ሠራተኛው የተመደበለትን የምርት ዕቅድ በነጠላም ሆነ በወል ከታቀደው በላይ ማምረት ሊችል ወይም ሠራተኛው ባለው ዕውቀት በነጠላም ሆነ በወል ፋብሪካውን ከወጪ ሊያድን በነጠላም ሆነ በወል የሚሰጥ ልዩ ክፍያ ነው፡፡ 

2.10. ቦነስ (ጉርሻ)፡- ማለት አሠሪው በበጀት ዓመቱ ውስጥ ከታክስ በኋላ ከሚያገኘው ትርፍ ላይ ፋብሪካው ፈቅዶ ለሠራተኛው የሚሰጠው ገንዘብ ነው፡፡ 

2.11. ቶፕ አፕ ()፡- ማለት የማነቃቂያ ክፍያ አይነት ሲሆን አንድ ኦፕሬተር መደበኛ ማሽን መያዝ ከሚገባው በላይ ተጨማሪ እንዲይዝ/እንድትይዝ በፋብሪካው በጽሁፍ ተፈቅዶ ሲይዝ/ስትይዝ እንዲሁም ከመደበኛ ሥራው በተጨማሪ ሌላ የሥራ መደብን ሸፍኖ ወይም ሸፍና እንድትሠሪ በፋብካው በጽሁፍ ተፈቅዶ የሚከፈል ማለት ነው፡፡ ክፍያውም በተሠራባቸው ቀናቶች ብቻ ታስቦ ይሆናል፡፡ 

2.12. አዲስ የሥራ መደብ፡- ማለት ለፋብሪካው መስፋፋትና ዕድገት አስፈላጊነቱ በአሰሪው ሲታመንበተ ጽድቆ በሥራ ላይ እንዲውል የሚደረግ የፀደቀ አዲስ የሥራ መደብ ነው፡፡ 

2.13. ፈቃድ፡- ማለት በዚህ ህብረት ስምምነት መሠረት ሠራተኛ በሥራ ቀን በሥራ ሰዓት ፈቃድ ከደመወዝ ጋር ወይም ያለደመወዝ ተፈቅዶለት በሥራ ገበታው ላይ የማይገኝበት ነው፡፡ 

2.14. ቅጣት፡- ማለት ሠራተኛው በዚህ የህብረት ስምምነት ወይም በመንግስት አዋጆችና ሌሎች ህጎችና ደንቦች ውስጥ ከተመለከተው የጥፋት ዓይነት አንዱን ፈጽሞ በመገኘቱ ለወደፊቱ እንዳይደገም የሚወሰድ የሥነሥርዓት እርምጃ ነው፡፡ 

2.15. የህብረት ስምምነት፡- ማለት በዕድገት ድርና ማግ የስፌት ክር አክስዮን ማህበርና በፋብሪካው መሠረታዊ ሰራተኛ ማህበር መካከል የተደረገ ስምምነት ነው፡፡ 

2.16. ደመወዝ፡- ማለት አንድ ሠራተኛ በሥራ ውሉ መሠረት ለሚያከናውነው ሥራ የሚከፈለው መደበኛ ክፍያ ነው፡፡ 

አንቀጽ 3

እውቅናን በተመለከተ

3.1. ፋብሪካው በአሰሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 እና የዚሁ ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 494/98 እና በዚህ ህብረት ስምምነት መሰረት የሰራተኛውን ህልውና እና የፋብሪካውን ዕድገት ለማስጠበቅ በባለቤትነት ለመምራት አሰሪው መብት ያለው መሆኑን የሠራተኛ ማህበሩ አውቆለታል፡፡  

3.2. በዚህ ህብረት ስምምነት መሠረት፡- ስለተመለከቱት አንቀጾች ስለሠራተኛው ጉዳዮች ከግል ክርክር በስተቀር ከፋብሪካው ጋር የህብረት ስምምነት ድርድር ለማድረግና ስለአጠቃላይ ሰራተኛ ጉዳይ ቀርቦ ማነጋገር የሚችለው የዕድገት ድርና ማግ የስፌት ክር አክሲዮን ማህበር መሠረታዊ ሠራተኛ ማህበር ብቻ መሆኑን አውቆ ፋብሪካው ተቀብሎታል፡፡ 

አንቀጽ 4

በዚህ ህብረት ስምምነት ያልተጠቀሱ ጉዳዮችን በተመለከተ

4.1. በዚህ ህብረት ስምምነት ያልተወሰነ ማህበሩንና ፋብሪካውን የሚመለከት ነጥብ ወይም ጉዳይ ቢያጋጥም ፋብሪካውና ማህበሩ ህግ በሚፈቅደው መሠረት በመነጋገር በሁለቱም ወገን ተቀባይነት ሲያገኝ እንዲጨመርና የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲያውቀው ወይም እንዲመዘገብ ያደርጋሉ፡፡ 

አንቀጽ 5

የዚህ ህብት ስምምነት ተፈፃሚነት ወሰን

5.1. ይህ የህብረት ስምምነት በዕድገት ድርና ማግ የስፊት ክር አክሲዮን ማህበር ውስጥ በአሰሪና ሠራተኛ መካከል በሚደረግ የዋና ክፍል የሥራ መደብንና ከዚያ በታች ባሉ የሥራ መደቦች ቅጥር ላይ በተመሠረተ የሥራ ግንኙነት ላይ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡ 

5.2. የሥራ መሪዎች ማለትም በህግ ወይም በአሠሪው በተሰጠው ስልጣን መሠረት የፋብሪካውን ዋና ዋና ተግባሮች በቀጥታ የሚያከናውኑ የመምሪያ ኃላፊዎችንና፣ ከዚህ በላይ የሆኑ የሥራ መሪዎችን (ኃላፊዎችን) እንዲሁም እነዚህን የሥራ አመራር ጉዳዮች አስመልክቶ የአሰሪውን ጥቅም ለመጠበቅ አሰሪው መውሰድ ስለሚገባው እርምጃ በራሱ የውሣኔ ኃሳብ የሚያቀርብ የህግ አገልግሎት ኃላፊውንም ጭምር የዚህ ህብረት ስምምነት ተፈፃሚነት ወሰን እነዚህን አካሎች አያካትትም፡፡ 

አንቀጽ 6

የፋብሪካውና የሠራተኛ ማህበሩ ግንኙነት

6.1. በፋብሪካው ማኔጅመንትና ሠራተኛ ማህበር መካከል ያለው ግንኙነት ፋብሪካው የተቋቋመበትን ዓላማ ለማስፈፀም ተመካክረው በመስራት ፋብሪካውንና ሠራተኛውን ውጤታማ በማድረግ ላይ የተመሠረተ ይሆናል፡፡ 

ክፍል ሁለት

የተዋዋይ ወገኖ ግዴታዎች

አንቀጽ 7

የአሰሪ ግዴታ

7.1. ማንኛውም አሠሪ በሥራ ውሉ ከተመለከተው ልዩ ግዴታዎችና በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 12 ከተዘረዘሩት በተጨማሪ የሚከተሉት ግዴታዎች ይኖሩታል፡፡ 

7.2. ሠራተኞች በየወሩ ለማህበራቸው የሚያዋጡትን የአባልነት መዋጮ ፋብሪካው ከደመወዛቸው እየቀነሱ በ30 ቀን ውስጥ ለማህበሩ ገንዘብ ያዥ ወይም ማህበሩ በጽሁፍ ለሚወክለው በህጋዊ ደረሰኝ ግቢ ያደርጋል፡፡ 

7.3. የሠራተኛው የግል ማህደር በጥንቃቄ እንዲያዝ አስፈላጊውን ክትትል ያደርጋል፡፡ ተገቢውን እርምጃም ይወስዳል፡፡ 

7.4. ከአንድ የሥራ ቦታ ወደ ሌላ ሥራ ቦታ የሚዛወሩትን ሠራተኞች የቦታውን መስፈርት የሚያሟሉ ከሆነ በቦታው ሲያገኙ የሚችሉትን ማንኛውም ጥቅም መጠበቅ፡፡ 

7.5. የማስታወቂያ መለጠፊያ ቦታዎች ሠራተኛው ሊያይ በሚችልበት አካባቢ ፋብሪካው ያዘጋጃል፡፡ 

7.6. አሠሪ በሠራተኛ ጉዳይ በዕድገት፣ በዝውውር በሥነ ሥርዓት ርምጅ እና በሌሎ የሠራተኛ ጉዳዮች ላይ የሚወሰደውን ውሳኔ በኮፒ ለማህበሩ ያሳውቃል፡፡ 

አንቀጽ 8

የሠራተኛ ግዴታዎች

8.1. በዚህ ህብረት ስምምነት ስለ ስራ ውል የተጠቀሱትን በፋብሪካው ውስጥ በሥራ ላይ የሚውሉ ደንቦችን የድርጅቱ የሥራ መመሪያዎችን እና በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 በአንቀጽ 13 የተዘረዘሩትን በሙሉ ያከብራል ይፈጽማል፡፡ 

8.2. የፋብሪካው የምርት ውጤት በጥራትና በብዛት እንዲመረት የምርት ዕቅዱ ግቡን እንዲመታ መላ ችሎታውነን እንዲሁም መደበኛ የሥራ ሰዓቱን በአግባቡ ሥራ ላይ ያውላል፡፡ 

8.3. ሁልግዜም የራሱንና የድርጅቱን ሥምና ዝና ይጠብቃል፡፡ እንዲሁም የፋብካውን ምስጢር ለማይመለከታቸው ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች እንዲያውቁ አያደርግም፡፡ 

8.4. ማህበሩና ፋብሪካው በህብረት ስምምነት የተስማሙባቸውን የሥነ ሥርዓት ደንቦች ያከብራል፡፡ 

8.5. ሠራተኛው ፋብሪካው ባዘጋጀው የሰዓት መቆጣጠሪያ መዝገብ ወይም ፓንች ላይ ወደ ሥራ ሲገባ ይመዘገባል ወይም ፓንች ያደርጋል፡፡ የፋብሪካውን የስራ ሰዓትም አክብሮ በሥራ ላይ ይገኛል፡፡ 

8.6. ከህግና ከህብረት ስምምነቱ ውጪ እስካልሆነ ድረስ ፋብሪካው ባዘዘው ማንኛውም ቦታ ይሠራል፡፡ 

8.7. በፋብሪካውና በሠራተኛ ማህበር (ተወካይ) መካከል አለመግባባት የሚፈጥር የሐሰት ወሬ ከማውራት ይቆጠባል፡፡ 

8.8. ከፋብሪካው ደንበኞች ወይም ከማንኛውም ሰው መደለያ ወይም ጉቦ መቀበል የለበትም፡፡ 

8.9. ወደ ፋብሪካው ሲገባና ሲወጣ ለፍተሻ ይተባበራል፡፡ መታወቂያ ሲጠየቅ ያሳያል፡፡ 

8.10. የፋብሪካውን ንብረት ወይም ኃብት ለግሉ ወይም ለሌላ ሰው አገልግሎት አያውልም፡፡ 

8.11. በፋብሪካው ቅጥር ግቢ ውስጥ በሥራ ሰዓት ወይም በሰርቪስ አገልግሎት ላይ በማንኛውም ምክንየት መደባደብ፣ መዛትና መሣደብ እንዲሁም ማንኛውም አፀያፊ ድርጊት ከማድረግ ይቆጠባል፡፡ 

8.12. ፋብሪካው ካልፈቀደ በስተቀር በሥራ ቦታና ጊዜ ሰብሰባ መሰብሰብ ልዩ ልዩ እትሞችንና ጽሁፎችን ማስፈረሚያ ሊስቶችን ማደል መለጠፍ ፈጽሞ የተከለከለ መሆኑን አውቆ ማክበር አለበት፡፡ 

8.13. ህግ ሊያስገድድ ወይም ፋብካው በበቂ ምክንያት ሲጠይቅ ለጤና ምርመራ ፈቃደኛ ሆኖ መገኘት (ከኤች.አይ.ቪ) ምርመራ በስተቀር 

8.14. በአሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ 377/96 መሠረት ትርፍ ሰዓት ሥራ እንዲሰራ ሲጠየቅ የመስራት 

8.15. ሠራተኛ ሥራውን ለማከናወን የተሰጠውን የመገልገያ መሣሪያዎች የአደጋ መከላከያ ቁሳቁሶች በአግባቡ ይጠብቃል፡፡ የስራ ልብሱን ለብሶ ይሰራል፡፡ 

8.16. ሲጋራ ከተፈቀደው ቦታ ውጪ ማጤስ የለበትም፡፡ 

8.17. ያለፈቃድና ያለበቂ ምክንያት ከሥራ መቅረት ከሥራ ቦታ ላይ ተነስቶ መሄድ የማይመለከተውን የግል ሥራ በስራ ሰዓት መሥራት የለበትም፡፡ 

8.18. ራሱንም ሆነ የሥራ ጓደኞቹን አደጋ ላይ የሚጥል የድርጅቱን ጥቅም የሚነካ ሁኔታ ሲያጋጥመው ወዲያውኑ ለአሰሪው የማሳወቅ ግዴታ አለበት፡፡ 

አንቀጽ 9

የሠራተኛ ማህበሩ ግዴታዎች

9.1. ይህን የህብረት ስምምነት ወይም አዳዲስ የሥራ ሁኔታዎችን ለማሻሻል በሚመለከት አሰሪው ለውይይት ሲጠየቅ ይቀርባል፡፡ 

9.2. ሠራተኛ የፋብሪካውን ምርትና ምርታማነት እዲጎለብት የስራ መመሪያዎችንና ደንቦችን የህብረት ስምምነቱን እንዲያከብር አስፈላጊውን ድጋፍ ትምህርትና ቅስቀሳ ያደርጋል፡፡ 

9.3. ፋብሪካው የምርት ዕቅዱን እንዲመታ የተሻለ የአሰራር ዘዴን ለመጠቀም በየጊዜው የሚያወጣቸውን ደንቦች የሚጥስ የሚቃረን ወይም ሊገድብ የሚችል ማንኛውም ተግባር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከመፈፀም ይቆጠባል፡፡ 

9.4. ማህበሩ የሰራተኛ ጉዳዮችን አስመልክቶ በማስታወቂያ ለሠራተኛ ሲያሳውቅ ወይም ሲለጥፍ ለፋብሪካው በቅድሚያ ያሳውቃል፡፡ ከፋብሪካው ፍቃድ ካላገኘ ከመለጠፍ ይቆጠባል፡፡ ድርጅቱም በ10 ቀናት ውስጥ በጽሁፍ መፍቀድና አለመፍቀዱን ያሳውቃል፡፡ 

9.5. በህግ ወይም በዚህ የህብረት ስምምሰነት አሰሪው ያገኘውን ህጋዊ መብት የሚጥስ ወይም ሊገድብ የሚችል ማንኛውም ተግባር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ከመፈፀም ይቆጠባል፡፡ በአሰሪው ላይ ህገወጥ ተግባርም አይፈጽምም፡፡ 

9.6. ማህበሩ የፋብሪካው ዕቅድ አወጣጥና ተግባራዊነት ተገቢውን ድጋፍና ተሣትፎ ያደርጋል፡፡ 

9.7. ሠራተኛው የህብረት ስምምነቱን ትርጉምና አፈፃፀም በሚገባ እንዲረዳ ከድርጅቱ ጋር በመተባበር አስፈላጊውን ሁሉ ያደርጋል፡፡ 

9.8. በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 እና የዚህ ማሻሻያ 494/98 የተደነገጉትን ያከብራል፡፡ 

አንቀጽ 10

የፋብሪካው (የአሰሪው) መብቶች

10.1. በህግ በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅና በዚህ የህብረት ስምምነት የተሰጠውን መብት እስካልተቃረነ ድረስ አሰሪው ከሥራ ውሉ የተነሳ የሰራተኛውን የሥራ እንቅስቃሴ ክንውን የመከታተልና የመቆጣጠር፣ ሥራን የመምራት፣ የሥራ ዕቅድ የማውጣት፣ ሠራተኛን አዛውሮ የማሠራት፣ ሠራተኛን የማሰናበት ወይም የመቅጠር፣ የሥነ ሥርዓት (ዲስፕሊን) ማስከበሪያ እርምጃዎችን የመውሰድ፡፡ 

10.2. ለሥራና ለድርጅቱ እድገት ወይም ውጤታማነት የሚረዱ መመሪያዎችን የሥራ ዕቅድ የማውጣት ተግባራዊነቱንም የመቆጣጠርና የማስፈፀም፡፡ 

10.3. ድርጅቱ ለሥራ ይጠቅመኛል ያለውን ሠራተኛ የመቅጠር፣ የማሳደግ፣ የሠራተኛውን ጥቅም በማይነካ ሁኔታ ከቦታ ቦታ አዛውሮ የማሠራት፡፡ 

10.4. በዚህ ህብረት ስምምነትና በአዋጅ ቁጥር 377/96 እና በማሻሻያው አዋጅ ቁጥር 494/98 የተደነገጉትን የሥራ ሥርዓት እርምጃዎችን እራሱ አጣርቶ እርምጃ መውሰድ፡፡ 

10.5. በአሰሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 እና በማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 494/98 መሠረት የስራ ውልን የማቋረጥ፣ የሠራተኛ ቅነሣና እገዳ የማድረግ መብት አለው፡፡  

አንቀጽ 11

የሠራተኛ ማህበሩ መብቶች

11.1. በዚህ ህብረት ስምምነትና በአሰሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 እና የማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 494/98 ስለተመለከቱትም ሆኑ ሌሎች ከስምምነቱ ውጭ ሲያጋጥሙ ስለሚችሉ ማንኛውም የሥራ ሁኔታ ሠራተኛውን ወክሎ ከአሰሪው ጋር የመነጋገር መብት አለው፡፡ 

11.2. በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 115 የተመለከቱትን ተግባራት የማከናወን፡፡  

11.3. ድርጅቱ በዕድገት አወዳድሮ ለሚመድባቸው ሠራተኞች ማህበሩ ሠራተኛን ወክሎ ያገኛል፡፡ ሆኖም ድርጅቱ ከሠራተኛው መሃል የተሻለ ይሠራልኛል ብሎ ያመነበትን ያለ ውድድር ሊመድብ ይችላል፡፡  

11.4. ጠቅላላ ሠራተኛውን የሚመለከቱ ከህብረት ስምምነቱና ከአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ 377/96 ውጪ በድርጅቱ በኩል የሚወጡ መመሪያዎች ተግባራዊ ከመሆናቸው በፊት በቅድሚያ ማህበሩ እንዲያውቅ ይደረጋል፡፡ ማህበሩም ሊያምንበት ለተግባራዊነቱ ይተባበራል፡፡ 

11.5. በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ 377/96 መሠረት የሠራተኛ ቅነሣ በሚደረግበት ጊዜ ማህበሩ በአፈፃፀሙ የመሣተፍ መብት አለው፡፡ 

ክፍል ሦስት

የሥራ ውል ለማሻሻልና ከሥራ ውል የሚመነጩ መብትና ግዴታዎችን 

ለጊዜው ስለማገድ

አንቀጽ 12 

የሥራ ውል የሚሻሻልበት ሁኔታ 

12.1. የሥራ ውል የሚሻሻልበት ሁኔታ በአዋጅ ቁጥር 377/96 መሠረት ይሆናል፡፡ 

አንቀጽ 13 

ከስራ ውል የሚመነጩ መብትና ግዴታዎችን ለጊዜው ስለማገድ 

13.1. የሥራ ውል ለጊዜው ለማገድ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 18 መሠረት ተፈፃሚ ይሆናል፡፡ 

አንቀጽ 14

ቅጥር፣ ዕድገት፣ ዝውውር፣ ውክልናና ተጠባባቂነት

አንቀጽ 14

የሠራተኛ ቅጥር

14.1. ለተወሰነም ሆነ ላልተወሰነ ጊዜ የሚቀጠር ሠራተኛ የሥራው ዓይነት የሥራው ቦታ ለሥራው የሚከፈለው ደመወዝ መጠን የአከፋፈሉ ሁኔታና ጊዜ እና ውሉ ፀንቶ የሚቆይበት ጊዜ የሚዘረዝር ውል መያዝ ይኖርበታል፡፡ 

14.2. ማንኛውም አዲስ ተቀጣሪ ሠራተኛ የሙከራ ጊዜ 45 ተከታታይ ቀናት ይሆናል፡፡ 

14.3. በሙከራ ጊዜ ያለ ሠራተኛ የሙከራ ጊዜውን የጨረሰ ሠራተኛ መብትና ግዴታ ይኖረዋል፡፡   

14.4. ጊዜ የተቀጠረ ሠራተኛ ለሥራው ብቁ ካልሆነ አሠሪው ያለማስጠንቀቂያና ያለ ሥራ ስንብት ክፍያና ካሣ ክፍያ የሥራ ውሉን ሊያቋርጥ ይችላል፡፡ 

14.5. በአዲስ የሚቀጠር ሠራተኛ ለሥራ ብቁ ለመሆኑ የጤና የምርመራ ውጤት እንዲያመጣ ይደረጋል፡፡ ወጪውም በድርጅቱ ይሸፈናል፡፡ 

14.6. የሥራ ውል አመሠራረትና ይዘት በአዋጅ ቁጥር 377/96 መሠረት ይሆናል፡፡ 

14.7. የውጭ ሃገር ዜጎች ስለሚቀጠሩበት ሁኔታ በአዋጅ ቁጥር 377/96 መሠረት ይሆናል፡፡ 

14.8. በሙከራ ጊዜ ያለ ሠራተኛ እንደ ሥራ ቦታው አስፈላጊነት የአደጋ መከላከያ ቁሳቁስ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ሊሰጠው ይችላል፡፡ 

14.9. የአዲስ ሠራተኛ ቅጥር የሚፈፀመው ቅጥሩ እንዲፈጸም ለሥራ አስኪያጅ ቀርቦ ሲታመንበትና በዋና ሥራ አስኪያጅ ሲጸድቅ ነው፡፡

አንቀጽ 15

ዕድገት

15.1. አሠሪው በሥራ አፈፃፀሙ የተሻሸለውን ወይም ለድርጅቱ ውጤት ያመጣል ብሎ ያመነበትን ሠራተኛ ያለውድድር በዕድገት ሊመድብ ይችላል፡፡ 

15.2. የደረጃ ዕድገት የሚሰጠው አንድ የሥራ መደብ በልዩ ልዩ ምክንያት ክፍት ሲሆንና ቦታው በውድድር እንዲሟላ ለሥራ አስኪያጅ ቀርቦ ሲፈቀድና ይህም በዋና ስራ አስኪያጅ ሲፀድቅ ነው፡፡ 

15.3. ክፍት የሆነውን ቦታ ለማሟላት መጀመሪያ በፋብሪካው ውስጥ ማስታወቂያ ይወጣል፡፡ ብቁ የሆነ ሰው ከፋብሪካው ከሌለ ፋብሪካው ከውጭ ሊቀጥር ይችላል፡፡ 

15.4. አንድ ሠራተኛ ከደረጃው በታች ላለ የሥራ መደብ ሊወዳደር አይችልም፡፡ 

15.5. ፋብሪካው ክፍት የሆነውን የሥራ መደብ በውድድር የሚያሟላ ሲሆን ለዚህም የዕድገት ኮሚቴ ይኖረዋል፡፡ 

አንቀጽ 16

የዕድገት ኮሚቴ የሚከተሉት አባላት ይኖሩታል

  • የአስተዳደር መምሪያ ሥራ አስኪያጅ ሰብሳቢ  ሰብሳቢ 
  • ዕድገት የሚሰጥበት መምሪያ ኃላፊ  አባል 
  • ዕድገት የሚሰጥበት ዋና ክፍል ኃላፊ  አባል 
  • የሠራተኛ ማህበር ተወካይ  አባል 
  • የሠራተኛ ማህበር ተወካይ  አባል 
  • የሠራተኛ አስተዳደር ዋና ክፍል  ፀሐፊ (ድምጽ የሌለው)

አንቀጽ 17

ውድድር የማይደረግባቸው የሥራ መደቦች

17.1. ደረጃ አሥር የሥራ መደብና ከዚያ በላይ ያሉ የሥራ መደቦች ያለውድድር በፋብሪካው በቀጥታ የሚመደቡ ይሆናሉ፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ከዚህ የሥራ መደብና ደረጃ በታች ያሉ የሥራ መደቦችም ፋብሪካው ካመነበት በውድድር ወይም ያለውድድር በዕድገት መመደብ ይቻላል፡፡ 

አንቀጽ 18

የደረጃ ዕድገት አወሳሰን በተመለከተ

18.1. የሥራ መደቡን መመዘኛ የሚያሟሉ ተወዳዳሪዎች እንደ ሥራ መደቡ ባህሪ የጽሁፍ፣ የተግባር፣ የቃል እንዲሁም ከሶስቱ በሁለቱ ወይም በሶስቱም በመፈተን በዕድገት ኮሚቴው ተመዝና እድገቱ በአሸናፊው ይሰጣል፡፡ 

18.2. የሁለቱ ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ዕጩዎች ውጤት እኩል ሲሆን በአገልግሎትና በሥራ አፈፃፀም ብልጫ ላለው ይሰጣል፡፡ 

18.3. ለደረጃ ዕድገት የሚያበቃ ነጥብ በሥራ አፈፃፀሙ የአንድ ዓመት የሥራ አፈጻጸም የግምገማ ውጤት 2.5 እና ከዚያ በላይ የሆነ ሠራተኛን ይመለከታል፡፡ 

18.4. አንድ ሠራተኛ ከያዘው ደረጃ በውድድር በዕድገት ሲያልፍ ለሠራተኛው የሚሰጠው የደረጃ ዕድገት 

ሀ/ እድገት ያገኘበትን ደረጃ መነሻ ደመወዝ ይሆናል፡፡ 

ለ/ እድገት ያገኘበት መነሻ ደመወዝ በፊት ከያዘው ደመወዝ ያነሰ ወይም እኩል የሆነ እንደሆነ እድገት ያገኘበት ደረጃ ደመወዝ ወደ ጎን ካሉት ዕርከኖች በፊ ከሚያገኘው ደመወዝ ብልጫ ያለውን ዕርከን ያገኛል፡፡   

18.5. ፋብሪካው የሚያከናውናቸው ቅጥርና ዕድገት በፋብሪካው የደመወዝ እስኬል መሠረት ሲሆን ፋብሪካው በቀላሉ ተገቢውን ባለሙያ ሊያገኝ ለማይችለው የሥራ መደብ በድርድር ሊቀጥር ይችላል፡፡ 

18.6. የሠራተኛ ቅጥር፣ የደረጃ ዕድገትና ዝውውር ዝርዝር አሠራር በድርጅቱ መዋቅርና በአስተዳደር የሥራ መመሪያ መስፈርት መሠረት ተፈፃሚ ይሆናል፡፡ 

18.7. አንድ ሠራተኛ በዕድገት፣ በቅጥር ከተመደበ ጀምሮ በቦታው ለአንድ አመት ያህል ጊዜ ካልሠራ ወደሚቀጥለው ከፍ ያለ የስራ መደብ በዕድገት ሊወዳደር አይችልም፡፡ ሆኖም ከአንድ ዓመት በላይ አገልግሎት ያላቸው የተጠየቀውን መሥፈርት የሚያሟሉ ካልተገኙ የውስጥ ማስታወቂያውን በድጋሚ በማውጣት አንድ ዓመት ያልሞላቸው አዲስ ተቀጣሪዎችና ዕድገት ያገኙ ሠራተኞች ሊወዳደሩ ይችላሉ፡፡ ይህም የሚሆነው ድርጅቱ የቀረቡትን ተወዳዳሪዎች ቢመደቡ ለድርጅቱ ይጠቅማሉ ብሎ ካመነ ብቻ ነው፡፡ 

አንቀጽ 19

ዝውውር

19.1. ፋብሪካው ሲያምንበት ሠራተኛን ከአንድ ክፍል ወደ ሌላ ክፍል በተመሣሣይ ደረጃ አዛውሮ ሊያሰራ ይችላል፡፡ ሆኖም ለቦታው የሚገባውን የአደጋ መከላከያና ልብስ ይሰጠዋል፡፡ ነገር ግን ድርጅቱ በተመሣሣይ ደረጃ የሚያሰራው ስራ ከሌለው ከደረጃው ዝቅ አድርጎ ሥራ ያለበት ቦታ በመመደብ ሊያሰራው ይችላል፡፡ 

19.2. ማንኛውም ዝውውር ሲፈፀም ከወር በላይ የሚቆይ ከሆነ ቋሚ ወይም ጊዜአዊ መሆኑ ለሠራተኛው በጽሁፍ መግለጽ ይኖርበታል፡፡ 

19.3. ሠራተኛው ከተዛወረበት ቦታ ለመሥራት ፈቃደኛ ካልሆነ ድርጅቱ ጥቅሙን ጠብቆ ሊያሰናብተው ይችላል፡፡ ለማህበሩም በግልባጭ ያሳውቃል፡፡ 

አንቀጽ 20

ውክልና

20.1. ውክልና፡ ማለት አንድ የሥራ ኃላፊ በሥራ ጉዳይና በዓመት ዕረፍት በህመምና በሌሎች በተለያዩ ምክንያቶች በሥራ ገበታው ላይ ሳይገኝ ሲቀር የሥራ መደቡን ከያዘው የሥራ መደብ ጋር ደርቦ እንዲሠራ የሚደረግበት አሰራር ነው፡፡ የአወካከል ሥርዓቱም ከሚወከልበት የሥራ መደብ በታች ያለ ሠራተኛ በመምሪያው ኃላፊ ሲወከልና ይህም በሥራ አስኪያጅ ሊፀድቅ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡  

20.2. በውክልና ተመድቦ የሚሠራ ሠራተኛ ከተመደበበት ዕለት ጀምሮ ለ26 ቀንና ከዚያ በላይ ከሠራ የተኪውን የደሞዙን 25% አበል ያገኛል፡፡ ሆኖም ክፍያው በምንም መልኩ ከብር 300 (ሶስት መቶ) አይበልጥም፡፡ 

20.3. በዚህ ህብረት ስምምነት መሠረት የውክልና አበል የሚሰጠው ለደረጃ አስርና ከዚያ በላይ ላሉ የስራ መደቦች ይሆናል፡፡ ተወካዩ በስራ መደቡ ላይ በሚያደርሰው ድክመት ተጠያቂ ይሆናል፡፡ ሆኖም ውክልናው ከ6 ወር በላይ መብለጥ የለበትም፡፡ 

20.4. ከደረጃ አስር በታች ላሉ የሥራ መደቦች ክፍት በሚሆኑበት ጊዜ የሰራተኛው የክፍል ኃላፊ ሲያዘው ያለ ደብዳቤ ከሥራ መደቡ ጋር ደርቦ ይሰራል፡፡ ሆኖም ከአንድ ወር በላይ ቦታውን ደርቦ እንዲሰራ ከተደረገ በጽሑፍ መታዘዝ አለበት በጽሁፍ የተሰጠው ውክልና ከ6 ወር መብለጥ የለበትም፡፡ 

20.5. የውክልና ወይም የተጠባባቂነት ደብዳቤ በሥራ አስኪያጅ ፊርማ ለመምሪያና ለአገልግሎት ሰቺዎች ለተወካዩ እንዲደርስ ይደረጋል፡፡ 

አንቀጽ 21

ተጠባባቂ ስለመመደብ

21.1. አንድ የሥራ መደብ በሞት በዕድገት ወይም ሠራተኛው ለቆ በመሄዱ ምክንያት ክፍት ሲሆን ከፋብሪካው ውስጥ የስራ መደቡን መመዘኛ የሚያሟላ ሠራተኛን ድርጅቱ በተጠባባቂነት መድቦ ሲያሠራ ይችላል፡፡ 

21.2. በተጠባባቂነት ተመድቦ ለሚሠራ ሠራተኛ በቦታው ቢያንስ በወር 26 ተከታታይ የሥራ ቀን ከሠራ የተጠባባቂነት አበል ለሥራ መደቡ የሚከፈለውን ደሞዝ 25% ያገኛል፡፡ ሆኖም ክፍያው በምንም መልኩ ከብር 300 (ሶስት መቶ) አይበልጥም፡፡ 

21.3. በዚህ ህብረት ስምምነት መሠረት የተጠባባቂ አበል የሚሰጠው ለደረጃ አሥርና ከዚያ በላይ ላሉ የስራ መደቦች ይሆናል፡፡ 

21.4. በተጠባባቂነት የሚሠራውን ሠራተኛ ከ6 ወር በላይ ማሠራት አይቻልም፡፡ የተመደበው ሰው ለቦታው ብቁ ከሆነ በቀጥታ ቦታው ይሰጠዋል ብቁ ካልሆነ በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ቦታው በውድድር ወይም በምደባ መሟላት ይኖርበታል፡፡ 

አንቀጽ 22

የሥራ አፈጻጸም ምዘና

22.1. የሥራ አፈጻጸም ምዘና ሠራተኛው የተመደበበትን የሥራ መደብ እንዲያከናውን በተሰጠው የሥራ ዝርዝር መሠረት የአእምሮና የአካል ብቃቱን በመጠቀም የተሰጠውን ሥራ በአጥጋቢ ሁኔታ ማከናወኑን ለማወቅ የሚደረግ ግምገማ ነው፡፡ 

22.2. የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ውጤት ከዚህ ለሚከተሉት ዓላማዎች ይረዳል፡- 

ሀ. አጥጋቢ የሥራ አፈጻጸም ያገኘን ሠራተኛ ወደ ሚቀጥለው የሥራ ደረጃ ለማሳደግ፣ 

ለ. በሥራ አፈጻጸም ግምገማ መሠረት የደመወዝ ጭማሪ፣ የማበረታቻ ክፍያዎችን፣ የቦነስ ሥጦታን ለመወሰንና ለመደልደል እንዲያመች፣ 

ሐ. የሥራ ድክመት ያለባቸውን ሠራተኞች ለይቶ በማወቅ ችግራቸውን ተረድቶ የሥራ አፈፃጸማቸውን እንዲያሻሸሉ ለማድረግ፣ 

በሥራ ላይ ድክመት ያለበትን ሠራተኛ በሥልጠና ድክመቱን እንዲያሻሽል ለማድረግ፣  

22.3. እያንዳንዱ ሠራተኛ የሥራ አፈጻጸሙን እንዲያየውና እንዲፈርም ይደረጋል፣ የስራ አፈጻጸም ምዘናው በዓመት አንድ ጊዜ ይደረጋል፡፡ 

22.4. በሥራ አፈጻጸሙ ከአምስት ነጥብ 2.5 በታች ያመጣ ሠራተኛ ለዕድገትና ለተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች ተካፋይ አይሆንም፡፡ 

ክፍል አምስት

ትምህርት ስልጠና

አንቀጽ 23

ትምህርት

23.1. ሠራተኛው ለድርጅቱ የተሻለ ሥራና እድገት እራሱን ለማዘጋጀት በትርፍ ጊዜው ለመማር ሲጠይቅ አሠሪው የሙያ ምክር ይሰጣል፡፡ ለሚማርበት ትምህርት ቤትም የትብብር ደብዳቤ ይጽፍለታል፡፡ 

23.2. ድርጅቱ ለሥራው አስፈላጊ ነው ብሎ ካመነ ከፍሎ ሊያስተምር ይችላል፡፡ 

23.3. አንድ ሠራተኛ በፋብሪካው ወጪ ከተማረ ትምህርት እንዳጠናቀቀ በቀጣይ ሁለት ዓመት ፋብሪካውን የማገልገል ግዴታ አለበት፡፡ 

23.4. አንድ ሠራተኛ ሁለት ዓመት ሳያገለግል ቢወጣ ከተማረ በኋላ ያገለገለበት ጊዜ በንጽጽር (Proportion) ተሰለልቶ የተማረበትን ሂሳብ እንዲከፍል ይደረጋል፡፡ ይህም ከሚያገኘው ማንኛውም ክፍያ ይቀነሳል፡፡ ሆኖ ሲገኝ ሠራተኛው ከራሱ ቀሪውን ክፍያ ይከፍላል፡፡ ይህ ካልሆነም ሠራተኛ ውል የገባበትን ጊዜ የማገልገል ግዴታ አለበት፡፡ 

23.5. ለቋሚ ሠራተኞች ለብሔራዊ ፈታናዎች በግል ተምረው ለሚፈተኑ ሠራተኞች በሚያቀርቡት ማስረጃ ለአንድ ጊዜ የ3 ቀን ደመወዝ የሚከፈልበት ፈቃድ ይሰጣቸዋል፡፡ 


አንቀጽ 24

ስልጠና

24.1. ድርጅቱ ለሥራው ይጠቅመኛል ብሎ ካመነ ለሠራተኛው ወጪውን ሸፍኖ የስልጠና ዕድል ሊሰጥ ይችላል፡፡ 

24.2. የድርጅቱ ሠራተኛ በማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ወይም በሠራተኛ ማህበር ፌዴሬሽንና ኮንፌዴሬሽን በሚያዘጋጀው የሙያ ትምህርት ፕሮግራሞችና ስብሰባዎች ላይ ተካፋይ እንዲሆን በሚጠየቅበት ጊዜ ሥራን በማይበድል ሁኔታ ድርጅቱ ከክፍያ ጋር ፍቃድ በመስጠት ይተባበራል፡፡ 

24.3. ድርጅቱ አንድን ሠራተኛ ለሥልጠና ወደ ውጭ ሀገር ሲልክ የመጀመሪያ 6 ወር ሙሉ ደመወዙን ለተወካዩ ይከፍላል ወይም በባንክ ያስቀምጣለታል፡፡

ክፍል ስድስት

የሥነ ሥርዓት እርምጃ አወሳሰድና የቅሬታ አቀራረብ ሥነ ሥርዓት 

አንቀጽ 25

የሥነ ሥርዓት እርምጃ አወሳሰድ


25.1. በሠራተኛው ላይ የሚወሰድ የሥነ ሥርዓት እርምጃ ሆን ተብሎ ሠራተኛን ለመጉት የታለመ መሆን የለበትም፡፡ 

25.2. በዚህ ህብረት ስምምነት መሠረት አንድ ሠራተኛ በጥፋቱ ሲቀጣ የቅጣቱ ወረቀት ለሠራተኛው መድረስ አለበት፡፡ 

25.3. የቅጣቱና የማስጠንቀቂያ ዕድሜ ለአንድ ዓመት ይሆናል፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ቅጣቱም ሆነ ማስጠንቀቂያው በግል ማህደር የሚቀመጥ ሆኖ በበጀት ዓመቱ በሚያጠፋው ጥፋት እንደገና በአዲስ ይጀመራል፡፡ ሆኖም የሠራተኛው የቀድሞ ጥፋቶች በዕድገት ውድድር እንደ አንድ መመዘኛ ነጥብ ሊወሰድ ይችላል፡፡ /የሁለት ተከታታይ ዓመት ቅጣት በውድድር ወቅት በመመዘኛነት ይወሰዳል/፡፡ 

25.4. ማንኛውም ሠራተኛ መከለሉን ሳያውቅ ወይም ሳይሰማ የሥነ ሥርዓት እርምጃ (ቅጣት) ሊወሰድበት አይችልም፡፡ 

25.5. ኃላፊው የሥነ ሥርዓት እርምጃ ከመውለዱ በፊት ሠራተኛው በትክክል ማጥፋቱን ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ 

25.6. ማንኛውም ሠራተኛ ከመምሪያው ሥራ ጋር በተያያዘ ጥፋት መፈፀሙን የቅርብ አለቃው የጥፋቱን ዝርዝር በመግለጽ ፈርሞ ለአስተዳደር ይልካል፡፡ የአስተዳደር ሠራተኛውም በዚህ ህብረት ስምምነትና በአዋጅ 377/96 የተመለከቱትን የሥነ ስርዓት እርምጃዎች ይወስዳል፡፡ 

25.7. በፋብሪካው ቅጥር ግቢ ለሚፈፀሙ አጠቃላይ ጥፋቶችና የሥነ ሥርዓት ጉድለቶች ለአስተዳደር መምሪያ ሪፖርት ሲደርስ ወይም በመምሪያው ሲደርስበት የአስተዳደር መምሪያው አጣርቶ የሥነ ሥርዓት ርምጃ ሊወሰድ ይችላል፡፡ 

አንቀጽ 26

ያለማስጠንቀቂያ የሥራ ውል ስለማቋረጥ

26.1. በፋብሪካው ሰነዶች፣ በግል ማህደሮች፣ በሰዓት መቆጣጠሪያ ሰነድ ላይ፣ አስቀድመው የተፃፉትን እውነተኛ ነገሮች ሆንብሎ ለማጭበርበር እውነተኛውን ትቶ ሌላ ነገር የጨመረ የደለዘ፣ ያጠፋ፣ የሰረዘ፣ የቀየረ ወይም የፋብሪካውን ህልውና ለማሣጣት ሚስጥር ያባከነ፣ የሃሰት ማስረጃ ያቀረበ በውጤት ክፍያና ሰነዶች ላይ ሆን ብሎ ለመጥቀም ሀሰት የመዘገበ፡፡ 

26.2. ፋብሪካውን የሚጎዳ ፈንጂ ወይም ድምጽ የሌላው መሣሪያ ይዞ በፋብሪካው ቅጥር ግቢ የተገኘ፣ 

26.3. በኃላፊነት በተረከባቸው የፋብሪካው ንብረቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ፣ 

26.4. በፋብሪካው ቅጥር ግቢ ውስጥ ቁማር የሚጫወት፣ 

26.5. በፋብሪካው ቅጥር ግቢ ውስጥ ባልተፈቀደ ቦታ ሲጋራ ሲያጤስ የተገኘ፣ 

26.6. በፋብሪካው ዓርማና ማህተም አላግባብ የተጠቀመ ሠራተኛ፣ 

26.7. በኃላፊነት የተሰጠውን የፋብሪካ ንብረት ሆን ብሎ ያጎደለ፣ 

26.8. የፋብሪካውን ንብረት ደብቆ ሊያወጣ ሲል የተገኘ፣ 

26.9. ማንነቱን ለመደበቅ የሐሰት የምስክር ወረቀት ያቀረበና በግል ማህደር ያስቀመጠ ወይም እንዲቀመጥ ያደርገ፣

26.10. በፋብሪካው የውጭ መስመር መኪኖች ያልተፈቀደለትን ጭነነት ጭኖ የተገኘ፣ 

26.11. በሚያሽከረክረው መኪና የደረሰውን ግጭት በወቅቱ ለሚመለከተው ኃላፊ ያላሳወቀ ወይም የደበቀ ሾፌር፣ 

26.12 በማንኛውም ሁኔታ ውላቸው በተቋረጠ ሠራተኞች ስም መብትና ጥቅም ለራሱ ጥቅም ያዋለ ወይም አሣልፎ የሰጠ፣ 

26.13. በሠራተኛ ሰርቪስ ውስጥና መሣፈሪያ ስፍራ ፀብና አንባጓሮ በማስነሣት አገልግሎት እንዲታወክ ያደርገ፣ 

26.14. ከፋብሪካው ዕውቅና ውጪ ልዩ ልዩ እትሞችንና የማስፈረሚያ ሊስቶችን ማዞርና ማስፈረም የማስታወቂያ መለጠፊያ ላይ መለጠፍ ያለፈቃድ ስብሰባ መጥራት፣     

26.15. በፋብሪካው ቅጥር ግቢ ደብደባ የፈፀመ በማስረጃ ሲረጋገጥ፣ 

26.16. በወንጀል ተፈርዶበት ከ30 ቀን በላይ የታሰረ 

26.17. በፋብሪካውና በሰራተኛው ላይ የሐሰት ወሬ የነዛ ሕገወጥ አድማና አመጽ ያነሣሣ፣ 

26.18. የሥራ ቦታውን ትቶ የሄደ የጥበቃና የህክምና ሠራተኛ፣ 

26.19. በስራ ቦታ ወይም በፋብሪካው ውስጥ በስራ ሰዓት ተኝቶ የተገኘ ሠራተኛ፣ 

26.20. ሆን ብሎ የኤሌክትሪክና የቴሌፎን መገናኛ መስመር እንዳይሰራ አድርጎ የተገኘ፣ 

26.21ከባለ ጉዳይ ወይም ከሠራተኛው ላይ ጉቦ የተቀበለ ወይም የሰጠ፣ 

26.22. ሠራተኛው በሥራ ዝርዝሩ የተመለከተውን ሥራ ለመሥራት ችሎታ እያለው የማምረቻ መሣሪያና ጥሬ ዕቃ ተሟልተውለት ከተወሰነው የምርት ጥራት ዓይነትና መጠን በታች በተደጋጋሚ ያመረተ ወይም የሰራ፣ 

26.23. በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 ያለማስጠንቀቂያ ከሥራ የሚያሰናበቱትን የፈፀመና በዚህ ህብረት ስምምነት እንዲሠራ የታዘዘውን ሥራ ለመሥራት ፈቃደኛ ያልሆነ ሠራተኛ፡፡ 

አንቀጽ 27

በማስጠንቀቂያ የሥራ ውል ስለማቋረጥ

27.1. በአሠሪው አነሣሽነት በማስጠንቀቂያ የሚደረግ የስራ ውል መቋረጥ በአሰሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 መሰረት ተፈፃሚ ይሆናል፡፡ 

27.2. በሠራተኛው አነሣሽነት በማስጠንቀቂያ የሚቋረጥ የሥራ ውል በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 መሰረት ተፈፃሚ ይሆናል፡፡ 

27.3. በሌላ ሁኔታ በአሠሪውም ሆነ በሠራተኛው አነሳሽነት የሚደረግ የሥራ ውል መቋረጥ በአዋጅ ቁጥር 377/96 እና በማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 494/98 መሠረት ተፈጻሚ ይሆናል፡፡  

አንቀጽ 28 

ደረጃ በደረጃ የሥነ ሥርዓት እርምጃ የሚሰሰጥባቸው ጥፋቶችና የቅጣት ዓይነቶች 

28.1. ከዚህ በታች በደረጃ የሚወሰደው የሥነ ሥርዓት እርምጃ አንዱ ለአንዱ ተወራራሽ አይሆንም፡፡ 

ተ.ቁ

የጥፋቱ ዓይነት

የቅጣቱ መጠንና ጥፋት

1ኛ ጥፋት

2ኛ ጥፋት

3ኛ ጥፋት

4ኛ ጥፋት

5ኛ ጥፋት

6ኛ ጥፋት


ያለፈቃድ ወይም ያለበቂ ምክንያት የሥራ ቦታውን ትቶ የሄደ ወይም በግቢው ውስጥ ሲዘዋወር የተገኘ

የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ 

የ1 ቀን ደመወዝ 

የ2 ቀን ደመወዝ 

የ5 ቀን ደመወዝ 

ከስራ ስንብት



ያለፈቃድ ወይም ያለበቂ ምክንያት ከስራ 1 ቀን የቀረ 

የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ 

የ2 ቀን ደመወዝ 

የ3 ቀን ደመወዝ 

የ5 ቀን ደመወዝ

1/3 የወር ደመወዝ 

ከሥራ ስንብት 


ያለፈቃድ ወይም ያለበቂ ምክንያት ከስራ 2 ቀን በተከታታይ የቀረ 

የ1 ቀን ደመወዝ 

የ3 ቀን ደመወዝ 

የ5 ቀን ደመወዝ 

1/3 የወር ደመወዝ 

ከሥራ ስንብት 



ያለፈቃድ ወይም ያለበቂ ምክንያት ከሠራ 3 ቀን በተከታታይ የቀረ 

የ2 ቀን ደመወዝ 

የ4 ቀን ደመወዝ 

የ5 ቀን ደመወዝ 

1/3 የወር ደመወዝ 

ከሥራ ስንብት 



ያለፈቃድ ወይም ያለበቂ ምክንያት ከሥራ 4 ቀን በተከታታይ የቀረ  

የ3 ቀን ደመወዝ 

የ5 ቀን ደመወዝ 

የ6 ቀን ደመወዝ 

1/3 የወር ደመወዝ 

ከሥራ ስንብት 



ያለፈቃድ ሰዓቱን አስሞልቶ ሥራውን ትቶ ከፋብሪካው ቅጥር ግቢ ውጭ የሄደ 

የ10 ቀን ደመወዝ 

የ15 ቀን ደመወዝ 

የአንድ ወር ዕገዳ 

ከሥራ ስንብት 




ያለፈቃድ ወይም ያለበቂ ምክንያት ከሥራ ሰዓት ከ20-30 ደቂቃ ዘግይቶ የገባ ወይም ቀድሞ የወጣ 

የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ 

የ1 ቀን ደመወዝ 

የ2 ቀን ደመወዝ 

የ3 ቀን ደመወዝ 

የ5 ቀን ደመወዝ 

ከሥር ስንብት 


በሥራ ሰዓት እንዲጠቀምበት የተሰጠውን የሥራ ልብስና የአደጋ መከላከያ አድርጎ የማይሰራ ሰራተኛ 

የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ 

የ1 ቀን ደመወዝ 

የ2 ቀን ደመወዝ 

የ5 ቀን ደመወዝ 

ከሥራ ስንብት



በሥራ ላይ ሆኖ ለበላዮቹ ወይም ለበታቾቹ ህገወጥ ፀባይ የሚያሳይ ሰራተኛ 

የ2 ቀን ደመወዝ 

የ3 ቀን ደመወዝ 

የ5 ቀን ደመወዝ 

ከስራ ስንብት 




በመጠጥ ወይም በአደንዛዥ ዕፅ ተመርዞ ወደ ሥራ የገባ ሠራተኛ ወደ ቤት እንዲመለሰ ሆኖ 

የ5 ቀን ደመወዝ 

የ10 ቀን ደመወዝ 

የ15 ቀን ደመወዝ 

ከሥራ ስንብት 




በአዋጅ ቁጥር 377/96 መሠረት ትርፍ ሰዓት እንዲሠራ ታዝዞ ከተስማማ በኋላ ያለበቂ ምክንያት የቀረ ወይም አልሰራም ያለ ሰራተኛ 

የ2 ቀን ደመወዝ 

የ3 ቀን ደመወዝ 

የ5 ቀን ደመወዝ 

1/3 የወር ደመወዝ 

ከሥራ ስንብት 



ሲገባ አልፈተሸም ያለ ሠራተኛ ወደ ስራ እንዳይገባ ይደረጋል፡፡ ከሥራ የሚወጣ አልፈተሽም ያለ ሠራተኛ ለህግ እንዲቀርብ ሆኖ 

የ3 ቀን ደመወዝ 

የ5 ቀን ደመወዝ 

1/3 የወር ደመወዝ 

ከሥራ ስንብት 




በሥራ ቦታ ላይ የበላይም ሆነ የበታች ሠራተኞችን የተሳደበ በማስረጃ ሲረጋገጥ 

5 ቀን ደመወዝ 

የ10 ቀን ደመወዝ 

የ15 ቀን ደመወዝ 

ከሥራ ስንብት 




በህጋዊ መንገድ መደበኛ ስራውን ለማከናወን እምቢተኛ ሆኖ የተገኘ 

የ2 ቀን ደመወዝ 

የ5 ቀን ደመወዝ 

የ15 ቀን ደመወዝ 

ከሥራ ስንብት 




የተሰጠውን ትዕዛዝ አላግባብ የፈፀመና ሥራውን ሆነ ብሎ ያበላሸ የንብረቱን ወቅታዊ ዋጋ ከፍሎ  

የ2 ቀን ደመወዝ 

የ5 ቀን ደመወዝ 

የ15 ቀን ደመወዝ 

ከሥራ ስንብት 




በፋብሪካው አጥር ዘልሎ ዘልሎ ወይም ሾልኮ መግባትና መውጣት  

1/3 የወር ደመወዝ 

ከሥራ ስንብት 






በኃላፊው እንዲሰራ የተሰጠውን የሥራ ትዕዛዝ ወይም መመሪያ ተቀብሎ ያለመፈፀም   

የ1 ቀን ደመወዝ 

የ2 ቀን ደመወዝ 

የ5 ቀን ደመወዝ 

የ6 ቀን ደመወዝ 

1/3 የወር ደመወዝ 

ከሥራ ስንብት 


ጥጥን ኬሚካልን ወይም ሌሎች ጥሬ ዕቃዎችን በግድየለሽነት ያባከነ   

በጥፋት ተጠያቂ ሆኖ የ1 ቀን ደመወዝ    

በጥፋቱ ተጠያቂ ሆኖ የ3 ቀን ደመወዝ 

በጥፋቱ ተጠያቂ ሆኖ የ5 ቀን ደመወዝ 

ከሥራ ስንብት 




የፋብሪካውን የግቢ ጽዳት በመፀዳዳት ወይም በመሳሰሉት የሚያበላሽ 

የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ 

የ1 ቀን ደመወዝ 

የ2 ቀን ደመወዝ 

የ5 ቀን ደመወዝ  

ከሥራ ስንብት 



ተረኛ ሆኖ በምድብ ሥራው ላይ የማይገኝ የጥበቃ፣ የጤና ባለሙያ፣ የኢንሹራንስ ወይም የሰርቪስ ሹፌር የእሳት አደጋ ሰራተኛ 

5 ቀን ደመወዝ 

የ6 ቀን ደመወዝ 

የ10 ደመወዝ 

ከሥራ ስንብት 




ለፍተሻ ሲጠየቅ መጥፎ ስነምግባር ያሣየ ሠራተኛ እንዲሁም የፍተሻ ሰራተኛ ሆኖ ያለአግባብ ያመናጨቀ 

የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ 

የ2 ቀን ደመወዝ 

የ5 ቀን ደመወዝ 

ከሥራ ስንብት 




በስራ ቦታ ላይ የሚያፌዝና እራሱ ስራ ፈትቶ ሌላውን ሥራ የሚያስፈታ ሠራተኛ 

የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ 

የ2 ቀን ደመወዝ 

የ5 ቀን ደመወዝ 

ከሥራ ስንብት 




የቅጣት ወረቀት የክስ ቻርጅ እና ሌሎችንም ሰነዶች ፈርሞ እንዲወስድ ሲጠየቅ ወይም እንዲፈርድ ሲጠየቅ ፍቃደኛ ያልሆነ 

የ2 ቀን ደመወዝና እስኪፈርም (እስኪወሰድ) ተግዶ ይቆያል 

የ5 ቀን ደመወዝና እስኪፈርም /እስኪወስድ ታግዶ ይቆያል/

የ7 ቀን ደመወዝ 

ከሥራ ስንብት 




የፋብሪካው ተሽከርካሪ ከተመደበለት ሥራ ውጪ ማዋል 

የ5 ቀን 

1/3 የወር ደመወዝ 

ከሥራ ስንብት 





በበዓል ዋዜማና ማግስት ያለበቂ ምክንያት ከሥራ የቀረ  

የ2 ቀን ደመወዝ 

የ3 ቀን ደመወዝ 

የ5 ቀን ደመወዝ 

ከሥራ ስንብት 




በሐሰት ሠራተኛን የከለለ ወይም እንዲከሰሰ ያደረገ 

የ2 ቀን ደመወዝ 

የ3 ቀን ደመወዝ 

የ4 ቀን ደመወዝ 

ከሥራ ስንብት 




የስራ ቦታውን ለተተኪው ሳያስረክብ የሄደና በሥዓት ያልተገኘ የጥበቃ የህክምና የእሳት አደጋ ሠራተኛና ሹፌር 

የ3 ቀን ደመወዝ 

የ5 ቀን ደመወዝ 

1/3 የወር ደመወዝ 

ከሥራ ስንብት 




በሐኪም የተሰጠውን መረጃ ሕክምናውን እንደጨረሰ በወቅቱ ያላቀረበ ሠራተኛ 

የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ 

የ1 ቀን ደመወዝ 

የ2 ቀን 

የ5 ቀን ደመወዝ 

ከሥራ ስንብት 



ፈቃድ ጠይቅ የክፍል አለቃው ሳይፈቅድለት ሥራውን ትቶ የሔደ ሠራተኛ  

የ1 ቀን ደመወዝ 

የ3 ቀን ደመወዝ 

የ5 ቀን ደመወዝ 

1/3 የወር ደመወዝ 

ከሥራ ስንብት 



ሠራተኛውንና ሥራውን የማይቆጣጠር የሥራ ኃላፊ 

የ3 ቀን ደመወዝ 

የ4 ቀን ደመወዝ 

የ5 ቀን ደመወዝ 

1/3 የወር ደመወዝ 

ከሥራ ስንብት 



እሁድ እና በበዓል ሥራ ታዝዞ ሥራ ያልገባ የእሳት አደጋ፣ ሹፌር፣ የኤሌክትሪክ፣ የውሃ ክፍል የጤና አገልግሎትና የሠዓት ቁጥጥር ሰራተኛ 

የ8 ቀን ደመወዝ 

የ10 ቀን ደመወዝ 

ከሥራ ስንብት 





ተተኪ ሠራተኛ ሳይገባለት ሥራ ትቶ የወጣ የእሳት አደጋ፣ ሹፌር፣ የኤሌክትሪክ ፣ የውሃ ክፍል፣ የጤና አገልግሎትና የሥዓት ቁጥጥር ሠራተኛ 

የ5 ቀን ደመወዝ 

የ6 ቀን ደመወዝ 

የ15 ቀን ደመወዝ 

ከሥራ ስንብት 



አንቀጽ 29

የቅሬታ አቀራረብ ሥነ ሥርዓት

29.1. ሠራተኛው የተወሰደበት የሥነ ሥርዓት እርምጃ ያ አግባብ ነው ብሎ ካመነ ቅሬታውን በ3 ቀን ውስጥ በማመልከቻ ለክፍል ኃላፊው ያቀርባል፡፡ 

29.2. የክፍል ኃላፊው በ2 ቀን ውስጥ በጽሁፍ ውሳኔ ይሰጠዋል፡፡ ሠራተኛው በክፍል ኃላፊው ውሳኔ ካልረካ በተዋረድ እስከ መምሪያ ኃላፊው ያመለክታል ሁሉም በ2 በ2 ቀን ጊዜ ውስጥ ውሳኔአቸውን ያሳውቃል፡፡ የመምሪያ ኃላፊው ውሳኔ የመጨረሻ ይሆናል፡፡ 

29.3. ማንኛውም ቅሬታ ከአንድ በላይ በተዘረዘረው ጊዜ ጠብቆ ካልቀረበ ተቀባይነት የለውም፡፡ 

29.4. ከሥራ ያለፈቃድ የቀረ፣ ያረፈደ፣ በሥራ ገበታው ላይ ያልተገኘ ሠራተኛን በክፍሉ ኃላፊ በሚያቀርበው የሥነ ሥርዓት እርምጃ መሠረት ድርጅቱ እርምጃ ይወስዳል፡፡ 

29.5. ያለፍቃድ ከሥራ የቀረን ሠራተኛ በማግስቱ የቀረቡትን ምክንያት ለክፍል ኃላፊው አሳውቆ ነፃ ፍቃድ ካልተሞላበት በአንቀጽ 29.4 መሰረት ተፈፃሚ ይሆናል፡፡ 

አንቀጽ 30

ቅጣትን ስለማሻሻል

30.1.ድርጅቱ ስለተወሰደው የሥነ ሥርዓት እርምጃ አጥጋቢና በቂ ነው ብሎ ካላመነ በሠራተኛው ላይ ተወሰደውን የሥነ ሥርዓት እርምጃ የማቅለል ወይም የመሠረዝ መብት አለው፡፡ 

ክፍል ሰባት

ስለ ሥራ ስንብት ክፍያና ካሳ

አንቀጽ 31

የሥራ ስንብት ክፍያ የሚሰጥበት ሁኔታ

31.1. የሙከራ ጊዜውን የጨረሰና በአዋጅ ቁጥር 377/96 እና በማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 494/98 መሠረት የስራ ውሉ የተቋረጠ ሠራተኛ በአዋጁ መሠረት የሥራ ስንብት ክፍያ የማግኘት መብት አለው፡፡ 

31.2. አንድ ሠራተኛ የሥራ ስንብት ክፍያ ከማግኘቱ በፊት ቢሞት የሥራ ስንብት ክፍያ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 110/2 ለተመለከቱት ጥገኞች ይከፈላል፡፡ 

አንቀጽ 32

የስራ ስንብት ክፍያ መጠን

ሀ/ ለመጀመሪያ የአንድ ዓመት አገልግሎት የሠራተኛው የመጨረሻው ሳምንት አማካይ የቀን ደመወዙን በሰላሳ ተባዝቶ ይከፈለዋል፡፡ ከአንድ ዓመት በታች ያገለገለ ሠራተኛ ግን እንደ አገልግሎት ጊዜው በንጽጽር እየተተመነ ተሠርቶ ይከፈለዋል፡፡ 

ለ/ ከአንድ ዓመት በላይ ያገለገለ ሠራተኛ በአንቀጽ 32.ሀ በተጠቀሰው ክፍያ ለእያንዳንዱ ተጨማሪ የአገልግሎት ዓመት የደመወዙ አንድ ሦስተኛ (1/3) እየታከለ ይከፈለዋል፡፡ ሆኖም ጠቅላላ ክፍያው ከአስራ ሁለት ወራት ደመወዙ መብለጥ የለበትም፡፡ 

ሐ/ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 24/4 እና አንቀጽ 29 መሠረት የሥራ ውል ሊቋረጥ በዚህ ህ/ስምምነት አንቀጽ 32.ሀ እና ለ ከተመለከተው በተጨማሪ የሠራተኛው የመጨረሻ ሳምንት የቀን ደመወዙ በ60 ተባዝቶ ይከፈለዋል፡፡ 

መ/ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ 1 (አንድ) መሠረት የሥራ ውሉን የሚያቋርጥ ሠራተኛ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 40 ከተመለከተው የሥራ ስንብት በተጨማሪ የመጨረሻ ሣምንት አማካይ የቀን ደመወዝ በ30 (ሰላሳ) ተባዝቶ ካሳ ይከፈለዋል፡፡ ይህም አግባብ ባለው ፍ/ቤት ሲወሰን የሚፈጸም ይሆናል፡፡ ይህ ድንጋጌ አግባብ ባለው የጡረታ ህግ በተሸፈነ ሠራተኛ ላይ ተፈጻሚ አይሆንም፡፡ 

አንቀጽ 33 

የምስክር ወረቀት አሰጣጥ 

33.1 አንድ ሰራተኛ የሥራ ውሉ ሲቋረጥ ክሊራንሱን አዙሮ ከጨረሰና መረጃው እንዲሰጠው ሲጠይቅ ወይም በሥራ ላይ እያለ ሥራ ልምድ እንዲሰጠው በደብዳቤ ሲጠይቅ የጠየቀው መረጃ ይጻፍለታል፡፡ 

33.2. አንድ የሥራ ልምድ ከተጻፈ በኋላ ሁለተኛ የሥራ ልምድ ለማጻፍ ቢያንስ 6 ወር መቆየት አለበት፡፡ 

33.3. የምስክር ወረቀት ወይም የሥራ ልምድ የሚከተሉትን ማካተት ይኖርበታል፡፡ 

ሀ. የሠራተኛውን ሥም  ሐ. የሥ ቦታው  ሠ. የሚያገኘው ደመወዝ

ለ. የሥራው ዓይነት  መ. የአገልግሎት ዘመን  ረ. የስራ ግብር መክፈሉን የሚገልጽ 

አንቀጽ 34

በሥ ምክንያት ስለሚመጡ ጉዳቶች ከሳ ክፍያ /ኢንሹራንስ/

34.1. በአዋጅ ቁጥር 377/96 እና በዚህ ህብረት ስምምነት መሠረት በሥራ ላይ የሚደርስ ጉዳት ማለት በሥራ ላይ የሚደርስ አደጋ ወይም ከሥራ ምክንያት የሚመጣ በሽታ ነው፡፡ ይኸም ከዚህ የሚከተሉትነን ይጨምራል፡፡ 

ሀ/ ሠራተኛው ከሥራ ቦታው ወይም ከመደበኛ የሥራ ሰዓት ውጪም ቢሆን የአሰሪውን ትዕዛዝ ስራ ላይ ያውል በነበረበት ጊዜ የደረሰ ጉዳት፡፡  

ለ/ ሠራተኛው ከቤቱ ወደ ስራ ቦታው ወይም ከሥራ ቦታው ወደ ቤቱ ሲጓጓዝ የደረሰ ጉዳት፡፡  

ሐ/ ሠራተኛው ሥራውን በማከናወን ላይ እያለ በድርጅቱ ወይም በሌላ ሶስተኛ ወገን ድርጊት ምክንያት የደረሰበት ጉዳት፡፡ 

34.2. በሥራ ላይ ለደረሰ ጉዳት የሚሰጠው የካሳ ክፍያ /ኃላፊነት ወሰን/ ፋብሪካው ለዚህ ጉዳት ከመድህን ድርጅት ጋር በገባው ስምምነት ወይም የመድህን ዋስትና ውል መሠረት ብቻ ነው፡፡ 

34.3. በዚሁ መሠረት የኢንሹራንስ መብት ያለው ሠራተኛ ለደረሰበት ጉዳት በ24 ሰዓት ውስጥ ለፋብሪካው ክሊኒክ ወይም በወቅቱ ላለ የሥራ ኃላፊ በማስመዝገብ በቀጣይ ሶስት ምስክሮችን አስመስክሮ ፈርመውበት ማቅረብ አለበት፡፡ ሠራተኛው በጉዳቱ አማካኝነት ሪፖርት ማድረግ ካልቻለ ቤተሰቡ ሪፖርት ማድረግ ይኖርበታል፡፡ በተወሰነው ጊዜ ያልተመዘገበ ጉዳት ተቀባይነት አይኖረውም፡፡  

34.4. በራሱ ላይ ሆን ብሎ ማንኛውንም ጉዳት ያደረሰ ሰራተኛ ፋብሪካው ኃላፊነት አይኖረውም፡፡ በተለይም በሚከተሉት ድርጊቶች የሚመጣ ጉዳት በራሱ ላይ ሆን ብሎ ያደረሰ ጉዳት ሆኖ ይቆጠራል፡፡ 

ሀ. አካሉን ወይም አእምሮውን ለመቆጣጠር በማይችልበት ሁኔታ በአደንዛዥ ዕጾች፣ በመጠጥ ደንዝዞ በሥራ ላይ መገኘት፣ 

ለ. በአሰሪው አስቀድሞ የተሰጠውን የሥራ ልብስና የአደጋ መከላከያዎች አለመጠቀምና የአደጋ መከላከያ ደንቦችንና መመሪያዎችን መጣስ፣ 

34.5. ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴሩ በሚያወጣው መመሪያ መሰረት በስራ ላይ የሚመጣ ጉዳት መድረሱን አግባብ ላለው አካል ድርጅቱ ማሳወቅ ይኖርበታል፡፡   

35.6. በድርጅቱ ሠራተኛ ላይ የደረሰው ጉዳት ሞት ወይም የአካል ጉድለት ያስከተለ ከሆነ ድርጅቱ የኢንሹራንስ ክፍያውን ለማስፈጸም እገዛ ያደርጋል፡፡ 

ክፍል ስምንት

አንቀጽ 35

የአደጋ መከላከያ የሥራ ልብስ አሰጣጥ

35.1. ፋብሪካው ለሠራተኛው እንደ ሥራው ባህሪ የሚያስፈልገውን የሥራ ልብስና የአደጋ መከላከያ ይሰጣል፡፡ 

35.2. ሠራተኛው ለሥራ ተብሎ የተሰጠውን የሥ ልብስ የአደጋ መከላከያ በመደበኛ የሥራ ሰዓቱ ምንጊዜም ለብሶ መገኘት አለበት፡፡ 

35.3. በማንኛውም ሁኔታ የሥራ ውሉ የተቋረጠ ሠራተኛ የሥራ ልብስ፣ ጫማ የአደጋ መከላከያ ቁሳቁስ ወዘተ አይሰጠውም፡፡ 

35.4. የአደጋ መከላከያና የሥራ ልብስ የሚያስፈልጋቸው 

ሀ. የምርትና ቴክኒክ መምሪያ ሠራተኞች በሙሉ 

ለ. የጥራት ቁጥጥር አገልግሎት ሠራተኞች በሙሉ 

ከአስተዳደር መምሪያ የትራንስፖርት፣ የጥበቃ፣ የክሊኒክ፣ የተላላኪና ጽዳት፣ የሰዓት ቁጥጥርና የመዝገብ ቤት ፐርሶኔክ ክለርክ ሠራተኞች

መ. ከንግድ መምሪያ የንብረት ክምችት ሠራተኞች፣ ጫኝና አውራጅ ሠራተኞች ይሆናሉ፡፡ 

ሠ. ከፋይናንስ መምሪያ ፔሮል ሠራተኞች ኮስትና በጀት ሠራተኞች የጠቅላላ ሂሳብ ሰራተኞች 

35.5. ፋብሪካው በአመት አንድ ጊዜ ለሠራተኞች በሃገር ውስጥ ባለሙያ የተሰፋ ጥራቱን የጠበቀ ከሃገር ውስጥ ምርቶች ከኮተን ወይም ከፖሊስተር ኮተን የተሰራ የሥራ ልብስ ወር በገባ በሐምሌ ወር የመስጠት ግዴታ ይኖርበታል፡፡   

ሀ. በዓመት፣ በሁለት ዓመት፣ በሶስት እና በአራት ዓመት ለሚታደሱ ሠራተኞች የአደጋ መከላከያ መገልገያዎች በሐምሌ ወር የሚታደል ይሆናል፡፡ 

ለ. ለወንድ ሠራተኞች ቱታ፣ 

ሐ. ለፈረቃ መሪዎች፣ ሱፐርቫይዘሮች፣ ፎርማኖች እና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ጋዋን፣ 

መ. ለጥበቃ ሠራተኞችና ለሹፌሮች ድርጅቱ በመረጠው ኮትና ሱሪ አስለክቶና አሰፍቶ እንዲሁም ሸሚዝና ቆዳ ጫማ፣ ለጥበቃ ሠራተኞች ከዚህ በተጨማሪ አርማ ያለበት ኮፍያ እንዲሁም የዝናብ ልብስ በ3 ዓመት አንድ፣ ካፖርት ከብርድ መከላከል የሚያስችል በ4 ዓመት አንድ እና የባትሪ ቀፎ በዓመት አንድ ጊዜ፣ ባትሪ ድንጋይ በዓመት 4 ጊዜ የባትሪ ቀፎ በዓመት አንድ ጊዜ ለምርት ፈረቃ መሪ ይሰጣል፣ 

ሠ. ለቢሮና ለፋብሪካው ሽንት ቤት ጽዳት ሠራተኞች ቆዳ ጫማና ለወንዶች ቱታ ለሴቶች ቀሚስና ፕላስቲክ ጓንት ይሰጣል፣ 

ረ. የቦይለር፣ የንብረት አስተዳደር ሠራተኛ፣ መካኒካል ወርክሾፕ፣ ኤልክትሪክ፣ እሣት አደጋና የጥገና ክፍል ሠራተኞችን በተመለከተ በሠራተኛና በማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥናት መሠረት ይሰጣል፡፡ ወደፊትም በጥናት ሚኒስቴሩ ለሚፈቅደው የሥራ መደቦች በጥናቱ መሠረት ይፈፀማል፡፡ 




ክፍል ዘጠኝ

አንቀጽ 36

ህክምና

36.1. ፋብሪካው ሠራተኛው ከደረሰበት ህመም ወይም በሽታ እንዲፈወስ በመጀመሪያ በግቢው ውስጥ ባለው ክሊኒክ ህክምና ይሰጣል፣ 

36.2. በሽታው ወደ ከፍተኛ ምርመራና ህክምና ሄዶ መታከም እንዳለበት በድርጅቱ ክሊኒክ ባለሙያ ሲረጋገጥ ድርጅቱ ሥምምነት ከአደረገባቸው የመንግስት ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች ሄዶ እንዲታከም ይደረጋል፡፡ 

36.3. ማንኛውም ሠራተኛ በዓመት ዕረፍት ፍቃድ ላይ እና በሌሎች የዕረፍት ቀናት በድንገት ቢታመም እንዲሁም ሴት ሠራተኛ ምጥ ይዟት ወደ ፋብሪካው ለመምጣት ባትችል በመንግስት ሆስፒታል ወይም ጤና ጣቢያዎች በአንዱ ታክመው ወይም ወልደው ደረሰኝ ሲያቀርቡ ይከፍላል፡፡ 

36.4. ሠራተኛው እንዲታከም የተላከበት ጤና ጣቢያ ወይም ሆስፒታል በሃገር ውስጥ በሚገኙ ሌሎች የመንግስት ጤና ጣቢያዎች ወይም ሆስፒታሎች ሄዶ እንዲታከም ማስረጃ ቢሰጠው ፋብሪካው ያሣክማል፡፡ ይህም የኤክስሬይ፣ የላብራቶሪ፣ የአልትራሣውንድ የመሳሰሉትን ያጠቃልላል፡፡ ሆኖም ያለሃኪም ፍቃድ ሠራተኛ በመረጠው የህክምና ማዕከል ሄዶ መታከም አይችልም፡፡ 

36.5. ራቅ ወዳለ አካባቢ በዓመት ዕረፍት በመሣሰሉት ፈቃዶች ሄዶ በህክምና ላይ እያለ ቢሞት በመንግስት ሆስፒታል ወይም ጤና ጣቢያ ለህክምና ያወጣውን ወጪ ህጋዊ ወራሾች በጠየቁ ጊዜ አሰሪው በደረሰኙ መሠረት አረጋግጦ ይከፍላል፡፡ 

36.6. ሠራተኛው ታሞ ሆስፒታል የተኛ እንደሆነ የ3ኛ ማዕረግ ወጪን ፋብሪካው ይሸፍናል ሶስተኛ ማዕረግ ከሞላ /ከሌለ/ በሁለተኛ ማዕረግ እንዲታከም ይደረጋል፡፡ የሶስተኛ ማዕረግ እያለ ሠራተኛው ፈልጎ በሌላ ማዕረግ የተኛ እንደሆነ የማዕረጉን ወጪ ልዩነት ሠራተኛው ይሸፈናል፡፡ ሆኖም በሽተኛው በተላከበት ሆስፒታል የ3ኛ ማዕረግ ካልተገኘ የበሽታው ሁኔታ ጊዜ የማይሰጥ መሆኑ በሃኪም ከተረጋገጠ 3ኛ ማዕረግ እስኪገኝ በተገኘው ማዕረግ ተኝቶ ይታከማል፡፡ 

36.7. ለሕክምና ወጪ ድርጅቱ 60% ሠራተኛው 40% ይሸፍናሉ፡፡ ይህም የአደጋ ሕክምናን አያካትትም፡፡ 

36.8. የድርጅቱ ጊዜአዊ ሠራተኞች የመጀመሪያ ደረጃ የድንገተኛ ህክምና 60% ድርጅቱ 40% ሠራተኛው ይሸፍናሉ፡፡ 

36.9. በድርጅቱ ውስጥ በሥራ ላይ እያለ ድንገተኛ አደጋ ወይም ህመም ሲደርስና በሌሊት ወደ ሌላ ሆስፒታል ሪፈር ለሚባል ሠራተኛ በደረሰኝ የሚወራረድ በክሊኒኩ ብር 500.00 /አምስት መቶ/ የሚሆን ገንዘብ እንዲቀመጥ ይደረጋል፡፡ 

አንቀጽ 37

የህክምና አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት

37.1. የፋብሪካው ክሊኒክ ለህክምና አገልግሎት 24 ሰዓት ክፍት ይሆናል፣ 

37.2. የህክምና ወይም የምርመራ አገልግሎት ሠራተኛው የሚያገኝበትን ዕለትና ሰዓት የፋብሪካው ክሊኒክ ፕሮግራም ይወጣል፣ 

37.3. ክሊኒኩ ባወጣው ፕሮግራም ተራ በመያዝ ካርዳቸውን አስወጥተው በሥነ ሥርዓት ክሊኒኩ ባወጣው ፕሮግራም መሠረት ተራ በመያዝ ካርዳቸውን አስወጥተው በሥነ ሥርዓት ወደ ሃኪም ይቀርባሉ፡፡ ሆኖም በሥራ ላይ አጣዳፊ ህመምና አደጋ ለደረሰባቸው ሠራተኞች ቅድሚያ ይሰጣል፡፡ 

37.4. በድንገተኛ ህመም ለህክምና ከሥራው ላይ ወደ ክሊኒክ የመጣ ሠራተኛ ህክምናውን እንደፈጸመ የክሊኒኩ ባለሙያ ሰዓቱን በቅጹ ላይ ሞልቶና ፈርሞ ለሠራተኛው ይሰጣል፡፡ ሠራተኛውም ወዲያውኑ ወደ ሥራ ተመልሶ ቅጹን ለቅርብ አለቃው ያስረክባል፡፡ ለአፈጻጸም የሚያመች ቅጽ ክሊኒኩ አዘጋጅቶ ሥራ ላይ ያውላል፡፡ 

37.5. ክሊኒኩ ለሠራተኛው የህመም ፈቃድ ሲሰጥ በዕለቱ ለክፍሉ ኃላፊና ለሰዓት ቁጥጥር ያሳውቃል፡፡ 

37.6. ሠራተኛው በሥራ ላይ እያለ ከሥራ የመነጨ አደጋ ቢደርስበት ለከፍተኛ ህክምና ወደ ሆስፒታል ለማድረስ እና መመለስ የማይችል ከሆነ ለመመለሻ ትራንስፖርት አገልግሎት ይሰጣል፡፡ 

37.7. የፋብሪካው ክሊኒክ በክሊኒክ ደረጃ በክምችት ሊኖረው የሚገባውን መድሃኒት ገዝቶ ይይዛል፡፡ ታማሚው ሠራተኛ ሃኪም ያዘዘለትን የመድሃኒት ማዘዣ በማምጣት መድሃኒቱ በክሊኒኩ ካለ ይወስዳል፡፡ መድሃኒቱ በክሊኒክ ከሌለ ከመንግስት መድሃኒት ቤቶች መድሃኒቱን ገዝቶ እንዲጠቀም ይደረጋል፡፡ መድሃኒቱ በመንግስት መድሃኒት ቤቶች አለመኖሩ በህክምና ባለሙ ከተረጋገጠ ወይም ክሊኒኩ ከሌላ ቦታ እንዲገዛ ሊፈቅድ ከማንኛውም መድሃኒት ቤት ሊገዛ ይችላል፡፡ 

37.8. በሥራ ላይ በደረሰ ጉዳት ሙሉ ህክምና ይሰጣል፡፡ የጉዳት ካሣ የሚያሰጥ ከሆነ በህክምና ቦርድ ሲረጋገጥ ፋብሪካው በኢንሹራንስ ድርጅት ጋር በገባው ውል መሠረት የጉዳት ካሳ ክፍያ ይከፍላል፡፡ 

37.9. በሥራ ላይ ወይም በሥራ ምክንያት ለደረሰ ጉዳት ሠራተኛው በህክምና ላይ ለሚያጠፋቸው ጊዜያቶች ፋብሪካው የሚከተለውን ክፍያ በደመወዝ ፋንታ ይከፍላል፣ 

ሀ. ለመጀመሪያው ሶስት ወራት የወር ደመወዙን 100%

ለ. ለሚቀጥለው ሶስት ወራት የወር ደመወዙን 75%

ሐ. ለሚቀጥሉት 6 ወራት የደመወዙን 50% ይከፍላል፡፡ 

37.10. በአንቀጽ 37.9 ሥር የተጠቀሰው ክፍያ ከዚህ በሚከተሉት ምክንያቶች በማንኛውም ዕለት ያቆማል፡፡ 

ሀ. ሠራተኛው የደረሰበት ጊዜያዊ ጉዳት የተወገደለት መሆኑ በሃኪም ሲረጋገጥ 

ለ. ሰራተኛው ሥራ መሥራት ካልቻለ ጡረታ ወይም ዳረጎት ማግኘት ከጀመረበት ቀን ጀምሮ 

ሐ. ሠራተኛው ሥራ መሥራት ካቆመበት ቀን ጀምሮ 12 ወራት ሲሞላው፡፡ 

37.11. አንድ ሠራተኛ በሥራ ምክንያት በደረሰበት አደጋ ወይም ህመም ተገቢው ህክምና ተደርጎለት እስከ መጨረሻው የማይድን መሆ ወይመ ለተቀጠረበት ሥራ ብቁ ያለመሆኑ በሐኪሞች ቦርድ ሲረገጋገጥ የሚገባው ተከፍሎት ከሥራው ይሰናበታል፡፡ 

ክፍል አስር

አንቀጽ 38

የትራንስፖርት አገልግሎት

38.1. ድርጅቱ ለሥራ መግቢያ መውጪያ በተወሰነው ሰዓት ለሠራተኛው የትራንስፖርት አገልግሎት ይሰጣል፡፡ 

38.2. የፋብሪካው ሰርቪስ መበላሸቱ በአስተዳደር መምሪያ ተረጋግጦ በማስታወቂያና በተለያየ መልኩ ሲገለጽ ሠራተኛው ወደ ሥራ ቦታ ለመምጣትም ሆነ ከሥራ ቦታ ወደ ቤቱ ለመሄድ ለ3 ቀን የመተባበር ግዴታ አለበት፡፡ 

38.3. ፋብሪካው የተበላሸውን የሰርቪስ መኪና በተቻለ መጠን አስጠግኖ አገልግሎት እንዲሰጥ የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡ ሆኖም በ3 ቀን ውስጥ ትራንስፖርት የሚያቀርብ ከሆነ የትራንስፖርት ወጪውን በታክሲ ታሪፍ ዋጋ ድረጅቱ ይከፍላል፡፡   

38.4. የትራንስፖርት ሰርቪስ ያለ ማስታወቂያ ቢቋረጥ ሠራተኛው ለ1፡30 ሰዓት ላልበለጠ ጊዜ ቢያረፍድ ደመወዙ ይታሰብለታል፡፡ ሆኖም ከምሽቱ 6ሰዓት የሚገቡ ሠራተኞችን አይመለከትም፡፡ 

38.5. ከተለመደው ፊርማታ ውጪ አዲስ ፊርማታ ለመፍጠር ካልፈለገ ድርጅቱና ማህበሩ በሚስማሙት መሠረት ተፈጻሚ ይሆናል፡፡ 

39.6.  የትራንስፖርት አገልግሎት መሣፈሪያና መውረጃ ቦታዎች ከዚህ የሚከተሉት ይሆናሉ፡፡ 

ዊንጌት  ሳሪስ 

ጳውሎስ  ጎተራ 

ኮልፌ  መገናኛ  ጎፋ 

አየር ጤና  ጊዮርጊስ  ገነት ሆቴል 

መካኒሣ 

38.7. የሽሮ ሜዳና የሰሜን ገበያ ፊርማታዎች በዚህ የህብረት ስምምነት እንዲታጠፍ የተደረገ ሲሆን የዚህ መስመር ቋሚ ሠራተኞች የትራንስፖርት ክፍያ በከተማ ታክሲ ታሪፍ መሰረት ድርጅቱ ይከፍላል፡፡ 

38.8. ቁጥራቸው አነስተኛ ሲሆኑ ሠራተኞች ሲባል ሰርቪሱን ረዥም መንገድ የሚያስኬድ ሆኖ ሲገኝ ሰራተኞቹ በታክሲ እንዲመጡ ወይም እንዲሄዱ ሆኖ የትራንስፖርት ወጪውን በከተማው ታክሲ ታሪፍ መሠረት ድርጅቱ ይከፍላል፡፡ 

ክፍል አስራ አንድ

ደመወዝና ልዩ ልዩ ክፍያዎች

አንቀጽ 39

የደመወዝ አወሣሠን

39.1. የሠራተኛው የደመወዝ መነሻ መጠን የሚወስነው በፋብሪካው የደመወዝ ስኬል ወይም በቅጥር ውል፣ ወይም በህግ መሠረት ይሆናል፣ 

39.2. ድርጅቱ ትክክለኛና አንድ ዓይነት የደመወዝ ስሌት ለማስፈን የማንኛውም ሠራተኛ የአንድ ወር ደመወዝ በ26 የሥራ ቀን ላይ ተመሥርቶ የሚሰራ ይሆናል፡፡ 

39.3. በዚህ ህ/ስምምነት አፈጻጸም የሚከተሉት ክፍያዎች አንደ ደመወዝ አይቆጠሩም፡፡ የትርፍ ሰዓት፣ ልዩ ልዩ አበሎች፣ ዓመታዊ ጎርሻ፣ የተወካይ ወይም የተተኪነት አበል፣ የማበረታቻ ክፍያ እና የጉድለት ማሟያ፡፡   

አንቀጽ 40

የደመወዝ አከፋፈል ደንብ

40.1. ድርጅቱ ደመወዝ የሚከፈለው እ.ኤ.አ ወር በገባ በ28ኛው ቀን ሲሆን ይህ ቀን እሁድ ቀን ወይም በሕዝባዊ በዓል ቀን ከዋለ የመክፈያ ቀን አስቀድሞ በዋለው ቀን ይሆናል፡፡ 

40.2. በአንዳንድ ልዩ ልዩ ምክንያቶች የሠራተኛው ደመወዝ አስቀድሞ እንዲከፈል አስፈላጊ መሆኑ ማህበሩ በጽሑፍ ሲጠይቅና ማኔጅመንቱ ሲያምንበት ከተወሰነው የመክፈያ ጊዜ በፊት የሠራተኛውን ደመወዝ ሲከፍል ይችላል፡፡ 

40.3. ደመወዝ የሚከፈለው በቀጥታ ለሠራተኛው ሆኖ በልዩ ልዩ አስገዳጅ ምክንያቶች ቀርቦ ደመወዙን መቀበል ካልቻለ ቤተሰቡን ወይም የሥራ ባልደረባውን በጽሁፍ ሲወክል ውክልና ለተሰጠው ሰው ይከፈላል፡፡ 

40.4. መተላለፍ የሚገባው ደመወዝ ነክ መረጃ ወይም ሰነድ በቂ ካልሆነ ምክንያት ዘግይቶ ሲደርስ ሠራተኛው የሠራበትን ደመወዝ የማግኘት መብቱ የተጠበቀ ሆኖ በጥፋተኛው ላይ የሥነ ሥርዓት እርምጃ ይወስዳል፡፡ 

40.5. ደመወዝ የሚከፈለው በሥራ ቀንና በፋብሪካው ቅጥር ግቢ ውስጥ ነው፡፡ 

40.6. በህግ፣ በፍ/ቤት ትዕዛዝ በዚህ ህብረት ስምምነት ወይም ሠራተኛው ሲስማማ ካልሆነ በስተቀር አሠሪው ከሠራተኛ ደመወዝ ሲቀንስ ወይም ሊያቻችል አይችልም፡፡ የሚቀነሰው የገንዘብ መጠንም ከሠራተኛ ደመወዝ 1/3 መብለጥ የለበትም፡፡ 

40.7. ሠራተኛው ደመወዙን በሚቀበልበት ጊዜ የደመወዙን መጠን የሚገልጽና የተቀናሽ ደመወዙን የሚያብራራ ሰነድ አሰሪው አዘጋጅቶ ይሰጣል፡፡ በአሠራሩ ቅር ያለው ሠራተኛ ሲገኝ አሰሪው ማስረዳትና ስህተት መኖሩ ሲረጋገጥ ከሶስት ቀን ባበለጠ ጊዜ ውስጥ አስተካክሎ መክፈል አለበት፡፡  

40.8. ሠራተኛው ለመሥራቱ ዝግጁ ሆኖ ሳለ ለሥራው የሚያስፈልገው ጥሬ ዕቃና መሣሪያ ሳይቀርብለት በመቅረቱ ወይም በሠራተኛው ችግር ባልሆነ ምክንያት ሣይሰራ ቢውል ደመወዙን የማግት መብት አለው፡፡ ሆኖም ድርጅቱ ሠራተኛውን አስፈላጊ በሆነበት ቦታ ለጊዜው አዛውሮ ማሠራት ይችላል፡፡

40.9. ሁሉም የድርጅቱ ቋሚና ጊዜአዊ ሠራተኞች ደመወዝ የሚከፈለው ወር በገባ በ28ኛው ቀን አንድ ጊዜ ብቻ ይሆናል፡፡ 

አንቀጽ 41 

የውጤት ክፍያ 

41.1. የውጤት ተከፋይ የሚባሉት በውጤት በሚከፈልበት መኪና /ማሽን/ ላይ ተመድበው ባመረቱት ምርት መጠን ተሰልቶ የሚከፈላቸው ሠራተኞች ናቸው፡፡ 

41.2. ማንኛውም የውጤት ተከፋይ ሠራተኛ በዓመት ፍቃድ በወሊድ ፍቃድ በአደጋ ፍቃድ ወዘተ.. የሚከፈለው ክፍያ በሥራ መደቡ በተሰጠው መደበኛ የወር ደመወዝ መሠረት ነው፡፡ 

41.3. በመደበኛ የውጤት ተከፋይ ሠራተኛ በሚሠራበት መኪና ላይ ተጠባባቂ ሠራተኛ ተመድቦ ቢሰራ በሥራው ውጤት መሠራት ክፍያ ያገኛል፡፡ 

41.4. የውጤት ክፍያ ወደፊት ፋብሪካው በሚያወጣው ዝርዝር አሠራር መሠረት የሚፈጸም ይሆናል፡፡ 

41.5. አንድ ሠራተኛ በውጤት ክፍያ ሲሰራ የውጤት ክፍያው ከደመወዙ በታች ከሆነ በውጤቱ መሠረት ይከፈለዋል፡፡ ይህ የሚሠራው የኢንሴንቲቭ ሲስተም ሲዘረጋ ነው፡፡ 

አንቀጽ 42

ቦነስ ወይም የደመወዝ ጭማሪ

42.1. ለሠራተኛው የሚሰራው የደመወዝ ጭማሪ የፋብሪካው ዓመታዊ የምርት ውጤት እንቅስቃሴ ወጪና ገቢ ተገናዝቦ ከብር 1,000,000.00 /አንድ ሚሊዮን ብር/ ያላነሰ የተጣራ ትርፍ መገኘቱ ዕውቅና ባለው የውጭ ኦዲተር ሲረጋገጥ የትርፉን 8 የደመወዝ ጭማሪ ለሠራተኛው ይሰጣል፡፡ አፈጻጸሙም ፋብሪካውና ሠራተኛ ማህበሩ በደረሱበት ስምምነት መሠረት ተፈጻሚ ይሆናል፡፡ 

42.2. ቦነስ ወይም የደመወዝ ጭማሪ የሚሰጠው በበጀት ዓመቱ ከ9ወር በላይ ለሠራ ሠራተኛ ነው፡፡

4.2.3. ከአንድ ሚሊዩን በላይ ለሚገኝ የተጣራ ትርፍ ድርጅቱና ማህበሩ በሚደርሱበት ስምምነት መሠረት ቦነስ ይሰጣል፡፡

አንቀጽ 43

ልዩ ልዩ የአበል ክፍያዎች

43.1. የውሎ አበል ክፍያ፣ ማለት ሠራተኛው ከመደበኛ ሥራ ቦታው ከአዲስ አበባ ከተማ ክልል ውጭ ወደሆነ ሌላ የሥራ ቦታ ሥራ እንዲያከናውን በፋብሪካው ሲታዘዝ በሄደበት ቦታ ለሚያጋጥመው የምግብ የመኝታና ሌሎች ጥቃቅን ወጪዎች እንዲሸፈን የሚደረግ ክፍያ ነው፡፡ 

43.2. የውሎ አበል ክፍያው የትራንስፖርት ወጪን አይሸፍንም የትራንስፖርት ወጪው በመንገድ ትራንስፖርት ታሪፍ መሠረት በሚያቀርበው ደረሰኝ/ሪሲት መሠረት የሚወራረድ ይሆናል፡፡ 

43.3. ፋብሪካው ለሠራተኛው የውሎ አበል የሚከፍለው ክፍያ ከዚህ እንደሚከተለው ይሆናል፡፡

 

ተ.ቁ 

የደመወዙ እስኬል 

የቀን አበል 


እስከ 500.00ብር ለሆነ 

ብር 90 


ከብር 501-1000ብር ለሆነ 

ብር 100 


ከብር 1001-1500ብር ለሆነ 

ብር 115 


ከብር 1501-2000ብር ለሆነ 

ብር 130


ከብር 2001-3000ብር ለሆነ

ብር 150





ከብር 3000 ብር በላይ ለሆነ 

ብር 175



43.4. የውሎ አበሉ ለቤትም ከዚህ በሚከተለው መሠረት ተተንትኖ ይከፈላል 

  • ለቁርስ  15%  እስከ ጥዋቱ 2ሰዓት ድረስ ባለጊዜ ለሥራ ከተላኩ 
  • ለምሳ  25%  እስከ 6 ሰዓት ድረስ ባለጊዜ ለሠራ ከተላኩ 
  • ለዕራት  25%  ከምሽቱ 2 ሰዓት በኃላ ወደ አ.አ. ለሚገቡ 
  • ለአልጋ  35% ከቤተት /ከአ.አ/ ውጪ ሄደው ካደሩ 


43.5. ሠራተኛው በአዲስ አበባ ክልል ውስጥ ለስልጠናም ይሁን ለሴሚናር ሲላክ ለትራንስፖርት በታሪፍ መሠረት እና የምሳ አበል ብቻ በስሌቱ መሠረት ይከፈላል፡፡ የምሳ ወጪው በአሰልጣኙ ድርጅት የሚከፈል ከሆነ ለትራንስፖርት ብቻ ይሰጠዋል፡፡  

43.6. ከአዋሽ መገንጠያ ጀምሮ መካከለኛው አዋሽና ተንዳሆ ላይኛው አዋጅ ጅቡቲ ጋምቤላ ኦሞ እርሻ ልማት ጊቤ እርሻ ልማት ለሥራ ሲሔድ የአበሉ 50% የበረሃ አበል ከአበሉ በተጨማሪ ይከፈለዋል፡፡ 

43.7. ከኢትዮጵያ ውጪ ለሥራ መላኩ በመንግስት ታሪፍ መሠረት የሚከፈል ይሆናል፡፡ 

አንቀጽ 44

ለገንዘብ ያዥ የሚሰጥ የመጠባበቂያ ገንዘብ

44.1. ለዋና ገንዘብ ያዥ ለገንዘብ ጉድለት ማካካሻ ብር 150 በወር ይከፈላል 

44.2. በደመወዝ መክፈል ወቅት የሠራተኞች የደመወዝ መክፈያ ቢል በማደል ለሚያስከፍሉ ሁለት ሠራተኞች ለእያንዳንዳቸው ብር 75.00 በወር ይከፈላል፡፡ 

44.3. ፋብሪካው ለገንዘብ ያዥ እንዲከፈል የወሰነው ወርሃዊ ክፍያ የመጀመሪያው 12 ወራት በሠራተኛው ሥም በመጠባበቂያ ገንዘብ መልክ ያጠራቅማል ከዚህ በኋላ ግን የመጠባበቂያ ገንዘብ ከፍያውን በየወሩ ለገንዘብ ያዥ ይከፍላል፡፡ 

44.4. ከገንዘብ ያዥ ላይ በኦዲተር ወይም በሂሳብ ኃላፊው የተረጋገጠ የገንዘብ ጉድለት ሲገኝበት ፋብሪካው በገንዘብ ያዥ ስም ካጠራቀመው መጠባበቂያ ገንዘብ ተቀናሽ በማድረግ ጉድለቱን ወዲያውኑ ያሟላል፡፡ ጉድለቱ ከመጠባበቂያው ገንዘብ በላይ ከሆነ ገንዘብ ያዡ/ዣ/ በአስቸኳይ ልዩነቱን ወዲያውኑ እንዲያስገባ /እንድታስገባ/ ይደረጋል፡፡ 

44.5. ገንዘቡን በተራ ቁጥር 44.4 መሠረት ማሟላት ካልቻለ /ካልቻለች/ ከከፋይነት የሥራ መደብ ታግዶ /ታግዳ/ በህግ ይጠየቃል /ትጠየቃለች/ ወይም ተገቢው የሥነ ሥርዓት እርምጃ ይወሰድበታል /ይወሰድባታል/፡፡ 

44.6. ገንዘብ ያዥ ከፋብሪካው በተለያየ ምክንያት ከሥራ ሲሰናበት /ስትለሰናበት/ ወይም ወደሌላ የሥራ ቦታ ሲዛወር /ስትዘዋወር/ በስሙ /በስሟ/ የተጠራቀመው ገንዘብ በአንድ ጊዜ ይከፈለዋል /ይከፈላታል/፡፡ 

አንቀጽ 45

የፈጠራ ሥራ ማሻሻያ ሃሳብ አቀራረብና የማትጊያ ክፍያ ሥርዓትን በተመለከተ

45.1. የሥራ ውድድርና የሥራ ፈጠራ ማሻሻያ ሃሳብ አቀራረብና የማትጊያ ክፍያ ስርዓት (Incentive Scheme) በተመለከተ በየደረጃው በሠራተኛውና በሥራ ኃላፊው መካከል የሥራ ውድድር መኖር ለፋብሪካው የምርት ዕቅድ አፈጻጸም ውጤታማነት ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑን ፋብሪካው ያምናል፡፡ 

45.2. ይህም የፈጠራ ሥራ ማሻሻያ ሃሳብ አቀራረብና የማትጊያ ክፍያ ሥርዓት ፋብሪካው አጥንቶ ወይም አስጠንቶ በሚያቀርበው የአሰራርና የአፈጻጸም መመሪያ መሠረት ተፈጻሚ ይሆናል፡፡ 

ክፍል አስራ ሁለት

የሥራ ሰዓት፣ የትርፍ ሰዓት፣ የሳምንት የዕረፍት ቀንና የህዝብ በዓላት

አንቀጽ 46

የፋብሪካው መደበኛ የሥራ ቀን ወይም የሣምንቱ የሥራ ሰዓት

46.1. የማንኛውም ሠራተኛ መደበኛ የሥራ ሰዓት በቀን ከ8ሰዓት ወይም በሣምንት ከ48ሰዓት መብለጥ የለበትም፡፡ 

46.2. ፋብሪካው እንደ ሥራው ፀባይ ሥራውን በቀን ፈረቃ፣ በምሺ ፈረቃና በሌሊት ፈረቃ /ሶስት/ ፈረቃ ከፍሎ ያሠራል፡፡ 

46.3. በቀን ፈረቃ ወይም በመደበኛ የሥራ ሰዓት ለሚሠሩ ሠራተኞች የሥራ ሰዓት ከሰኞ እስከ አርብ ባሉ የሥራ ቀኖች ጧት ከ2ሰዓት እስከ 6ሰዓት ከሰዓት በኋላ ከ7ሰዓት እስከ 10ሰዓት ቅዳሜ ከ2ሰዓት እስከ 6ሰዓት ይሆናል፡፡ 

46.4. በፈረቃ/በሽፍት/ ለሚሠሩ ሠራተኞች የሥራ ሰዓት ከሰኞ እስከ ቅዳሜ፡-

ሀ. ለጠዋት ገቢ ከጥዋቱ 2፡00 /ሁለት ሰዓት/ እስከ ምሽቱ 6፡00 /ስድስት ሰዓት/

ለ. ለ10ሰዓት ገቢ ከቀኑ 10፡00 /አስር ሰዓት/ እስከ ምሽቱ 6፡00 /ስድስት ሰዓት/

ሐ. ለሌሊት ገቢ ከምሽቱ 6፡00 /ስድስት ሰዓት/ እስከ ጥዋቱ 2፡00 /ሁለት ሰዓት/ ይሆናል፡፡ 

46.5. በፈረቃ ለሚሠሩ ሠራተኞች ለምግብ መመገቢያ በስራ ሰዓት መካከል 30 ደቂቃ ይኖራቸዋል፡፡ ይህም የምሣ ሰዓት ምርትን ለማያደናቅፍ መልኩ በፋብሪካው የክፍል ኃላፊዎች ይደለደላል፡፡ 

46.6. የፋብሪካው የሥራ ፀባይ ሲያስገድድ ወይም ከፋብሪካው አቅም በላይ የሆነ ችግር ሲያጋጥም የሣምንቱን የሥራ ሰዓት በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 62፣63፣64 መሠረት ማደላደል ይቻላል፡፡ 

አንቀጽ 47

የሣምንቱ የዕረፍት ቀን

47.1. ማንኛውም ሠራተኛ በሰባት ቀናት /በሣምንት/ ጊዜ ውስጥ ያልተቆራረጠ ከ24 ሰዓት የማያንስ የዕረፍት ቀን ያገኛል፡፡ 

47.2. በተቻለ መጠን የማንኛውም ሠራተኛ የሣምንት የዕረፍት ቀን እሁድ ቀን ይሆናል፡፡ ሆኖም ከሥራ ፀበይና የአገልግሎት አሰጣጥ የተነሳ የጥበቃ ሠራተኞችን አይመለከትም፡፡

47.3. በአንቀጽ 47.2. ለተጠቀሱ ሠራተኞች በሣምንቱ የሥራ ቀኖች በአንዱ በማደላደል በተከታታይ ከ24 ሰዓት የማያንስ የዕረፍት ቀን ያገኛሉ፡፡ 

47.4. በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 71 መሠረት የተገለጹት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ በሣምንቱ የዕረፍት ጊዜ ማሠራት ይቻላል፡፡ ሆኖም ክፍያው በትርፍ ሰዓት አከፋፈል ሥርዓት መሠረት ይፈጸማል፡፡ የትራንስፖርት አገልግሎት እንደ አስፈላጊነቱ ይሰጣል ወይም የትራንስፖት ክፍያ በታክሲ ሂሳብ ይከፈላል፡፡ 

አንቀጽ 48

የትርፍ ሰዓት ክፍያ

48.1. በዚህ ህብረት ስምምነት መሠረት ከተወሰነው መደበኛ የሥራ ሰዓት በላይ የሚሠራ ሥራ የትርፍ ሰዓት እንደሆነ ይቆጠራል፡፡ 

48.2. የትርፍ ሰዓት ሥራ እንዲሠራ የሚደረገው በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 67 መሰረት ነው፡፡ 

48.3. ከመደበኛ የሥራ ሰዓት ውጪ ለሚሠራ የትርፍ ሰዓት ስር ለሰራተኛ የሚከፈለው በሚከተለው መሰረት ይሆናል፡፡ 

ሀ. ከንጋቱ 12ሰዓት እስከ ምሽቱ 4ሰዓት ለሚሠራ የትርፍ ሰዓት ስራ ለመደበኛ የስራ ሰዓት የሚከፈለው ደመወዝ በአንድ ሩብ (1¼) ተባዝቶ 

ለ. ከምሽቱ 4ሰዓት እስከ ንጋቱ 12ሰዓት የሚሰራ የትርፍ ሰዓት ሥራ ለመደበኛ ሥራው በሰዓት የሚከፈለው ደመወዝ በአንድ ተኩል (1½) ተባዝቶ

ሐ. በሣምንት የዕረፍት ቀን የሚሠራ የትርፍ ሰዓት ሥራ ለመደበኛው ሥራው በሰዓት የሚከፈለው ደመወዝ በሁለት /2/ተባዝቶ

መ. በሕዝብ በዓላት ቀን ለሚሠራ የትርፍ ሰዓት ስራ ለመደበኛ ሥራው በሰዓት የሚከፈለው ደመወዝ በሁለት ተኩል /2½/ ተባዝቶ ይከፈላል፡፡ 

48.4. የትርፍ ሰዓት ክፍያ ለደመወዝ መክፈያ በተወሰነው ቀን ከደመወዝ ጋር ይከፈላል፡፡ 

48.5. የትርፍ ሰዓት ክፍያ የሚከፈላቸው የፈረቃ ኃላፊ /ሽፍት ሊደርና/ ከዚያ በታች ላሉ የሥራ መደቦች ይሆናል፡፡ 

48.6. ከደረጃ አስራ አንድ በላይ ከመምሪያ ኃላፊ በታች ላሉ የሥራ መደቦች ከመደበኛ የሥራ ሰዓታቸው ውጪ የሠሩበት ሰዓት በማካካሻ ተይዞላቸው በሌላ ጊዜ እንዲያርፉበት ይደረጋል፡፡ የሠሩት ሰዓትም በበላይ ኃላፊያቸው ፊርማ ተረጋግጦ በሰዓት ቁጥጥር እንዲቀመጥ ይደረጋል፡፡ የሰዓት ቁጥጥርም ያረፈበትን ሰዓት እየተከታተለ ተቀናሽ ያደርጋል፡፡ 




አንቀጽ 49

የህዝብ በዓላት

አግባብ ባለው ህግ መሠረት የሚከበሩ የሕዝብ በዓላት ከዚህ የሚከተሉት ይሆናሉ፡፡

49.1. በወር ደመወዝ የሚከፈለው ሠራተኛ በህዝብ በዓላት ባለመሥራቱ ምክንያት ከደመወዙ አይቀነስበትም፡፡ 

49.2. አንድ የህዝብ በዓል ከሌላ የህዝብ በዓል ጋር ተደርቦ ወይም በአዋጅ ቁጥር 377/96 መሠረት ወይም በማንኛውም ልዩ ህግ በተወሰነ የዕረፍት ቀን ላይ ወይም በዚህ ህ/ስምምነት በተወሰነው የዕረፍት ቀን ላይ ቢውል ለዚህ ቀን የሠራ ሠራተኛ ክፍያ የሚያደርግበት በአንዱ የህዝብ በዓል ብቻ ይሆና፡፡ 

49.3. የፋብሪካውን የምርት ሂደት ለመጠበቅ ሲባል በህዝብ በዓል ቀን ማሠራት አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝና በፋብሪካው ሲታዘዝ ሠራተኛው የመሥራት ግዴታ አለበት፡፡ ይህንንም የፋብሪካው አስተዳደር አስቀድሞ በማስታወቂያ ይገልጻል፡፡ ክፍያውም በህዝብ በዓል ክፍያ ስሌት መሠረት ይፈፀማል፡፡ 

አንቀጽ 50

የትርፍ ሰዓት ክፍያ የማይከፈልበት ሥራ

ሀ. የውሎ አበል የሚከፈለው ሠራተኛ በውሎ አበል ክፍያ ላይ እያለ፣ 

ለ. ለሥልጠና የሚላክ ሠራተኛ በሥልጠና ላይ እያለ፣ 

ሐ. በተተኪነት ወይም በውክልና ላይ ያለ ሠራተኛ፣  

ክፍል አስራ ሦስት

ልዩ ልዩ ፈቃዶችን በተመለከተ

አንቀጽ 51

የዓመት እረፍት /ፍቃድ/ መጠን

51.1. የዓመት እርፍት ፍቃድ የሚታሰበው ሰራተኛው የተቀጠረበትን ጊዜ መሠረት በማድረግ ነው፡፡ 

51.2. ለመጀመሪያ አንድ ዓመት ያገለገለ ሠራተኛ 14 የሥራ ቀን የዓመት ፍቃድ ይሰጠዋል፡፡ 

51.3. ከአንድ ዓመት በላይ ለሆነ አገልግሎት በ14 ቀን ላይ ለእያንዳንዱ ተጨማሪ ዓመት አንድ ተጨማሪ ቀን እየታከለ ይሰጣል፡፡ 

51.4. በዓመት ፍቃድ ላይ የሚገኝ ሰራተኛ የሚከፈለው ደመወዝ ሥራ ላይ ኖሮ ከሚከፈለው ጋር እኩል ይሆናል፡፡ 

51.5. ለዓመት ፍቃድ ብቁ የሚያደርገው ቀን ለመወሰን ሲባል በድርጅቱ ለ26 የሥራ ቀናት የሠራ ሠራተኛ ለአንድ ወር እንደሰራ ይቆጠራል፡፡ 

51.6. በዚህ ህ/ስምምነትና በአዋጅ ቁጥር 377/96 መሠረት የሥራ ውሉ የተቋረጠ ሠራተኛ ያልተጠቀመበት የዓመት ፍቃድ ታስቦ በገንዘብ ይከፈለዋል፡፡ 

51.7. አንድ ሠራተኛ ያገለገለበት ጊዜ ከአንድ ዓመት በታች ከሆነ በአገልግሎት ዘመኑ ልክ ተመጣጣኝ የሆነ የዓመት ፍቃድ በዚያው በአገከለገለበት ዓመት ይሰጠዋል፡፡ 

አንቀጽ 52 

የዓመት ፍቃድ አሰጣጥ 

52.1. አሠሪው የሠራተኛው የዓመት እረፍት የሚወጣበትን ቀን ፕሮግራም በማውጣት ይወሰናል፡፡ ይህም አሰሪው ሥራውን በተለመደው ሁኔታ ለመሥራ በሚያስችለው እና በተቻለ መጠን በሠራተኛው ፍላጎት ላይ የተመሠረቱ እንዲሆን ጥረት ያደርጋል፡፡ 

52.2. ፋብሪካው በሚያወጣው የዓመት እረፍት ፕሮግራም መሠረት በእያንዳንዱ ዓመት ለሠራተኛው የሚገባውን የዓመት ፍቃድ ይሰጣል፡፡ ሆኖም ሠራተኛው ያልታሰበና አጣዳፊ ችግር ሲያጋጥመውና ማኔጅመንቱ ሲፈቅድ ካለው እረፍት ላይ ቀንሶ ሊሰጠው ይችላል፡፡ 

አንቀጽ 53

የዓመት ፍቃድ ስለመከፋፈልና ስለማስተላለፍ

53.1. አንድ ሰራተኛ ሳይከፋፈል የሚሰጥ የዓመት ፍቃድ ከክፍያ ጋር ያገኛል ሆኖም ሠራተኛው ተከፋፍሎ እንዲሰጠው ሲጠይቅና አሰሪው ሲስማማ ለሁለት ተከፍሎ ወይም አጣዳፊ ችግር ሲያጋጥም ከ5 ቀን የማያንስ የዓመት ዕረፍት ሲሰጠው ይችላል፡፡   

53.2. አሠሪው የሥራ ሁኔታ ሲያስገድደው የሰራተኛውን የፈቃድ ጊዜ ሲያስተላልፍ ይችላል፡፡ 

53.3. አንድ ሠራተኛ በዓመት እረፍት ላይ እያለ የጋብቻ፣ የወሊድ፣ የሃዘን እንዲሁም የህመም ፍቃድ ቢያገኝ የዓመት እረፍቱ ጊዜ ባገኘው ፍቃድ መጠን ይራዘማል፡፡ 

53.4. ሠራተኛው የያዘው የሥራ መደብ ተተኪ የሚይገኝለት ከሆነና ጥያቄው በሥራ ክፍሉ ቀርቦ በሥራ አስኪያጅ ሲፈቀድ የዓመት እረፍቱ ሊራዘም ይችላል፡፡ ሆኖም የዓመት እረፍት ፍቃድ ከ2ዓመት በላይ ሊራዘም አይችልም፡፡ 

53.4. ሠራተኛው የያዘው የስራ መደብ ተተኪ የማይገኝለት ከሆነና ጥያቄው በሥራ ክፍሉ ቀርቦ በሥራ አስኪያጅ ሲፈቀድ የዓመት እረፍቱ ሊራዘም ይችላል፡፡ ሆኖም የዓመት እረፍት ፍቃድ ከ2 ዓመት በላይ ሊራዘም አይችልም፡፡ 

53.5. የዓመት ፍቃድን በመከልከል ወደ ገንዘብ ለውጦ መክፈል የተከለከለ ነው፡፡ ሆኖም ሠራተኛው ሊስማማና አሠሪው ለመክፈል ሲፈቅድ የዓመት ዕረፍቱን በገንዘብ ለውጦ መስጠት ይቻላል ይህም የሚሆነው የዓመት ዕረፍቱን ወደ ገንዘብ ለመለወጥ የሚያስችል የሥራ ችግር ሲያጋጥመው፡፡  

አንቀጽ 54

በፍቃድ ላይ ያለ ሠራተኛ ስለመጥራት 

54.1. በዓመት ፍቃድ ላይ ያለ ሠራተኛ ተጠርቶ እንዲሰራ ሊደረግ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 80 መሠረት ተፈጻሚ ይሆናል፣ 

አንቀጽ 55 

የጋብቻ ፍቃድ 

55.1. አንድ ሠራተኛ ለመጀመሪያ ጊዜ ህጋዊ ጋብቻ ሲፈጽም 3 ቀን ደመወዝ የሚከፈልበት 5 ቀን ደመወዝ የማይከፈልበት ነጻ ፍቃድ ያገኛል፡፡  

አንቀጽ 56 

የሃዘን ፍቃድ 

56.1. የሠራተኛው አባት፣ እና፣ ባል፣ ሚስት፣ ልጅ፣ ወንድም፣ እህት፣ የትዳር ጓደኛ እናት፣ አባት፣ ልጅ፣ ወንድም፣ እህት ሲሞት 3 የሥራ ቀን ደመወዝ የሚከፈልበት ፍቃድ 5 ቀን የማይከፈልበት ነጻ ፍቃድ ያገኛል፡፡ ስለ እርግጠኝነቱ ሠራተኛው ማስረጃ ከዕድር ወይም ከቀበሌ ማቅረብ ይኖርበታል፡፡ እንዲሁም ዕድር የሌለውና በቀበሌ ያልተመዘገበ ሠራተኛ ከላይ ከተጠቀሱት ዘመዶች ሲሞትበት ስለመሞቱ በሶስት ምስክሮች ሲረጋገጥ የሃዘን ፈቃድ ይሰጠዋል፡፡ ይህም በቤተሰቡ ዝርዝር ውስጥ ሲቀጠር ካለመዘገበው ውስጥ ሆነው ከተገኙ ነው፡፡ 

56.2. ከሠራተኛው ቤት ከተጠቀሰው ዝምድና ውቺ አስክሬን ቢወጣ 2 ቀን ከክፍያ ጋር ፈቃድ ያገኛል፡፡ 

56.3. የፋብሪካው ቋሚ ሠራተኛ በሞት በሚለይበት ጊዜ ለቀብር ማስፈጸሚያ የሚሆን ብር 3.000 /ሶስት ሺህ/ ለሠራተኛው ቤተሰብ አሰሪው ይከፍላል፡፡ አፈጻጸሙን ማህበር ተከታትሎ ያስፈጽማል፡፡ 

56.4. አንድ የፋብሪካው ቋሚ ሠራተኛ በሞት በሚለይበት ጊዜ በቀብር ስነሥርዓቱ ላይ የሚገኙ ከ10 ለማይበልጡ የፋብሪካው ሠራተኞች የ2 ሰዓት ደመወዝ የሚከፈልበት ፍቃድ ሥራ በማይበደልበት ሁኔታ ይሰጣል፡፡ አንድ የማጓጓዣ ሰርቢስም ይመደባል፡፡ 

አንቀጽ 57

ለማህበር ሥራ የሚሰጥ ፍቃድ

57.1. የሠራተኛ ማህበር መሪዎች የሥራ ክርክር ለማቅረብ፣ የሕብረት ስምምነት ለመደራደር፣ በማህበር ስብሰባ ለመገኘት፣ ለሴሚናሮችና በስልጠና ለመካፈል እንዲችሉ፣ የማህበሩን ሥራ ለማከናወን ማህበሩ በጽሁፍ ሲጠይቅና ማስረጃ ሲያቀርብ ፍቃድ ከደመወዝ ጋር ይሰጣል፡፡ 

57.2. የማህበር የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ስብሰባ ሥራን በማይበድል ሁኔታ በየ15 ቀን ከ3-6 ሰዓት ስብሰባ ያደርጋሉ የስብሰባ ቀኑንም በጽሁፍ ያሳውቃሉ፡፡ 

57.3. የማህበሩ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴና የምክር ቤት አባሎች በገቢ ውስጥ ለመሰብሰብ ሲፈልጉ ከ24ሰዓት በፊት ፋብሪካው በጽሁፍ ሲጠየቁ በ6 ወር አንድ ጊዜ ደመወዝ የሚከፈልበት ፍቃድ ይሰጣቸዋል፡፡ 

አንቀጽ 58

ልዩ ልዩ ተግባሮችን ለማከናወን ለሠራተኛ የሚሰጥ ፍቃድ

58.1. አንድ ሠራተኛ የሥራ ክርክር ለማሰማት፣ ወይም የአሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ ህጎችን ለማስፈጸም ስልጣን ያላቸው አካሎች ዘንድ ጉዳዩን ለማስማት ሲቀርብ በሚያቀርበው ህጋዊ ማስረጃ መሠረት ለዚሁ አላማ ላጠፋው ጊዜ ብቻ ከክፍያ ጋር ፍቃድ ይሰጣል፡፡ 

58.2 አንድ ሠራተኛ የሲቪል መብቱን ሲያስጠብቅ ወይም የሲቪል ግዴታውን ሊፈጽም በሚያቀርበው ህጋዊ ማስረጃ መሠረት ለዚሁ ዓላማ ላጠፋው ጊዜ ብቻ ከክፍያ ጋር ፍቃድ ይሰጠዋል፡፡ 

58.3. ማንኛውም ሠራተኛ ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ሲደርስበትና ይኸውም በአሰሪው ሲታመንበት የቅርብ አለቃውን ፍቃድ በመጠየቅ ከክፍያ ነፃ የሆነ ፍቃድ ይሰጠዋል፡፡ ሆኖም ሠራተኛው የዓመት ዕረፍት ካለውና ከዓመት እረፍቱ እንዲታሰብለት አስቀድሞ ከጠየቀና ይህም በአሰሪው ከታመነበት ወደ ዓመት እረፍት ሊቀየርለት ይችላል፡፡ ይህ የዓመት ዕረፍት ከአንድ ቀን በታች የሆነ ሰዓታን አይመለከትም፡፡ 

58.4. የክፍል አለቃው ከ5 ተከታታይ ቀን በላይ ከክፍያ ነፃ የሆነ ፍቃድ በአንድ ጊዜ መስጠት አይችልም፡፡ ከዚህ ጊዜ በላይ ነፃ ፍቃድ የሚያሰጥ ችግር ሊያጋጥም ማመልከቻው በክፍሉ ኃላፊ አስተያየት ተሰጥቶበት ይኸው በአስተዳደር መምሪያ ተቀባይነት ሲያገኝ ነፃ ፍቃድ ሊፈቀድለት ይችላል፡፡ 

አንቀጽ 59

የህመም ፈቃድ

59.1. ማንኛውም የፋብሪካው ቋሚ ሠራተኛ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በተከታታይ ወይም በተለያየ ጊዜ ከዚህ የሚከተለውን የህመም ፍቃድ ያገኛል፡፡ 

ሀ. ለመጀመሪያው ወር ከሙሉ ደመወዝ ክፍያ ጋር (100%)

ለ. ለሚቀጥሉት ሁለት ወራት ከደመወዙ ሃምሳ በመቶ ክፍያ ጋር (50%)

ሐ. ለሚቀጥሉት 3 ወራት የህመም ፍቃድ ክፍያ የማይፈጽምበት   

59.2. ከዚህ በላይ በአንቀጽ 59.1 ከፊደል ሀ-ሐ የተመለከውን የሕመም ቃድ መብቱን ጨርሶ ድኖ ወደ ሥራ ለመመለስ ያልቻለ ሠራተኛ ተገቢ መብቱን ጠብቆ አሠሪው የማሰናበት መብት አለው፡፡ 

59.3. የህመም ፍቃድ የጊዜ ገደብ የሚያገለግለው ለአንድ ዓመት ጊዜ ብቻ ሲሆን ዓመቱ ሲያልቅ የሕመም ፍቃድ ስሌት በአዲስ ከመሉ ደመወዝ ጋር ይጀምራል፡፡ 

59.4 የፋብሪካው ቋሚ ሠራተኛ ከሥራ ጋር በተያያዘ የመጣ ህመም መሆኑ በሃኪም ሲታመንበት በዓይኑ ላይ ጉዳት ቢደርስበት በሀኪም መነጽር ከታዘዘለት ድርጅቱ የመነጽርና የሕክምና ወጪውን ይሸፍናል፡፡ 

59.5. ማንኛውም የሐኪም ፍቃድ በፋብሪካው ክሊኒክ ኃላፊ ወይም ሪፈር በተደረገበት ተቋም ይሰጣል፡፡ የክሊኒኩ ኃላፊ ወይም በክሊኒክ ኃላፊ ተወካይ ሠራተኛ በሌለበት በማታ ሽፍት ጤና ረዳቶች ለ1 ቀን ፍቃድ መስጠት ይችላሉ፡፡ ሆኖም በተከታዩ ቀን ህመምተኛው ካልተሻለው ለሐኪም መቅረብ አለበት፡፡ 

59.6. በሕክምና ላይ እያለ በሌላ ምክንያት የሥራ ውሉ የሚቋረጠበት ቀን ጀምሮ ያለው የህመም ፍቃድ ክፍያ አይከፈለውም፡፡ 

59.7. የአንድ ሠራተኛ የህመም ፍቃድ ከጀመረበት ቀን አንስቶ በ12 ወራት ውስጥ በተከታታይ ወይም በተለያዩ ጊዜያት ቢወሰድም በማንኛውም ሁኔታ ከ6 ወር አይበልጥም፡፡ 

አንቀጽ 60

የወሊድ ፍቃድ

60.1. ነፍሰጡር የሆነች ሠራተኛ ከዕርግዝናዋ ጋር የተያያዘ ምርመራ ለማድረግ አሠሪው ከደመወዝ ጋር ፍቃድ ይሰጣታል፡፡ ሆኖም ሠራተኛዋ ከምርመራ ኃላፊ የሐኪም ማስረጃ ማቅረብ አለበት፡፡ 

60.2. ነፍስ ጡር የሆነች ሴት ከመውለዷ በፊት ሐኪም እንድታርፍ ካዘዘ ከክፍያ ጋር እረፍት ይሰጣታል፡፡ 

60.3. ነፍሰጡር የሆነች ሠራተኛ እወልዳለሁ ብላ ከገመተችው ቀን በፊት መውለጃዋ ሲደርስ የ30 ተከታታይ ቀን የወሊድ ፍቃድ እንዲሁም ስትወልድ ከወለደችበት ቀን ጀምሮ 60 ተከታታይ ቀናት የወሊድ ፍቃድ ከክፍያ ጋር ይሰጣታል፡፡ 

60.4. ሠራተኛዋ ከመውለዷ በፊት የወሰደችው የ30 ቀን ፍቃድ ሲያልቅ ካልወለደች እስከ ምትወልድበት ቀን ድረስ በአንቀጽ 60.2 መሠረት ዕረፍት ልታገኝ ትችላላች፡፡ የ30 ቀን ፍቃዷ ሣያልቅ የወለደች በዚህ አንቀጽ ንዑስ ቁጥር 3 መሠረት የምትወስደው ፍቃድ ይጀምራል፡፡ 

60.5. አንዲት ነፍሰጡር ሠራተኛ የ5 ወር ነፍሰጡር መሆኗ በህክምና ባለሙያ ሲረጋገጥ ወይም ሲታመንበት፣ 

ሀ. በጠዋት ፈረቃ ብቻ እንድትሠራ ይደረጋል፣

ለ. ሁልጊዜ ከመውጫ ሰዓት በፊት 10 ደቂቃ ቀድማ እንድትወጣ ይፈቀዳል፣ 

ሐ. የትርፍ ሰዓት ሥራ እንድትሰራ አትገደድም፣

መ. ነፍሰጡር ሴት ከምሽቱ 4ሰዓት 

60.6. አንዲት ነፍሰጡር ሠራተኛ ገንዘቧን ቀርባ መውሰድ ካልቻለች በጽሁፍ በምትወክለው ሠራተኛ አማካኝነት ገንዘቧን መውሰድ ትችላለች፡፡ 

60.7. ነፍሰጡር የነበረች ሠራተኛ የወለደችው ልጅ ታ ሆስፒታል ቢተኛ ሠራተኛዋ ለማስታመም ፍቃድ ከጠየቀች ድርጅቱ በሚፈቅድላት መሠረት የማይከፈልበት ነጻ ፍቃድ ታገኛለች፡፡ ሆኖም ህክምናው ሲጠናቀቅ ማስረጃ ማቅረብ ይኖርበታል፡፡ 

60.8. አንዲት ነፍሰጡር የሆነች ሠራተኛ በሥራ ውል ከተመለከተው ሥራ ውጪ ማሠራተ አይቻልም፡፡ ሆኖም ነፍሰጡሯ የምትሠራው ሥራ ለጤንነቷም ሆነ ለጽንሷ አደገኛ መሆኑ በሐኪም ሲረጋገጥ ለጤናዋ አስፈላጊ ባልሆነ ቦታ ተመድባ እንድትሰራ ይደረጋል፡፡ 

ክፍል አስራ አራት

ማህበራዊ አገልግሎትን በተመለከተ

አንቀጽ 61

61.1. ድርጅቱ ማንኛውም ሠራተኛ መደበኛ የጡረታ ጊዜው ከመድረሱ ከአንድ ዓመት በፊት ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርግ ለሠራተኛው ጡረታ የሚወጣበትን ጊዜ በጽሁፍ ያሳውቀዋል፡፡ 

61.2. አንድ መደበኛ የጡረታ መውጪያው የደረሰ ሠራተኛ አሠሪው በጽሁፍ ሲያሳውቀው አልቀበልም ማለት አይችልም፡፡ 

61.3. በዚህ የህብረት ስምምነት ስለ ዓመት ፍቃድ የተጠቀሰው ቢኖርም በጡረታ የሚገለል ሠራተኛ የመጨረሻ አንድ ዓመት እረፍት ፍቃዱን አጠራቅሞ በገንዘብ ተለውጦ ይሰጠዋል፡፡ ሆኖም ሠራተኛው የተለየ ችግር ገጥሞት የዓመት ፍቃዱን ሊጠቀምበት ቢፈልግ ሊጠቀምበት ይችላል፡፡ 

61.4. አንድ ሠራተኛ ጡረታ ከመውጣቱ በፊት የአበል መቀበያ ደብተሩ እንዲደርሰው ፋብሪካው በወቅቱ አስፈላጊውን ፎርማሊቲ አሟልቶ ለማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ያስተላልፋል፡፡ 

61.5. በማንኛውም ሁኔታ የሥራ ውሉ የተቋረጠ ሠራተኛ ፋብሪካውን ሲለቅ የጡረታ መዋጮ ያወጣውን እንዲመለስለት ሲጠይቅ ፋብሪካው የጡረታ ህጉ በሚፈቅደው መሰረት ተገቢውን መረጃ በማስተላለፍ ያስፈጽማል፡፡ 

61.6. የጡረታ ወራሾች የወራሽነት መብታቸውን በፍርድ ቤት አስወስነው ሲያቀርቡ ህጉ በሚፈቅደው መሠረት ይፈጸማል፡፡ 

አንቀጽ 62 

ማህበራዊ አገልግሎት 

62.1. የሠራተኛ ችግሮችን ለመቅረፍ ታስቦ ለሚቋቋም እንደ ዕድርና የገንዘብ ቁጠባ የመሳሰሉ አገልግሎቶች በፋብሪካውና በማህበሩ ስምምነት ሲደርስበት ተቀባይነት ይኖራቸዋል፡፡ 

62.2. የአስተዳደር መምሪያ የፋብሪካውንና የሠራተኛውን ደህንነት ለመጠበቅ የሚረዳ የማህበሩን የሚያሳትፍ አንድ የሴፍቲ ኮሚቴ ከሚመለከታቸው ክፍሎ በመሰየም ያቋቁማል፡፡ የተቋቋመው ኮሚቴ የተስማማበትንና መውሰድ የሚገባውን የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃ በፋብሪካው በሪፖርት መልክ ያቀርባል፡፡ ፋብሪካውም ተገቢውን እርምጃ ይወስዳል፡፡ 

62.3. ለሠራተኛው የቁጠባና የብድር አገልግሎት ማህበር በፋብሪካው ውስጥ ለጽህፈት ሥራ የሚገለገልበት ጽ/ቤት ይፈቀድለታል፡፡ 

ሀ. ከሠራተኞች ላይ የተሰበሰበው ገንዘብ በቀጣዩ 10 ቀን ውስጥ ማህበሩ ለወከለው አካል በህጋዊ ደረሰኝ ገቢ ያደርጋል፡፡ 

ለ. የቁጠባ ማህበሩ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ለመሰብሰብ ሲፈልጉ ድርጅቱን ሲጠይቁ ከ2 ሰዓት ያልበለጠ ጊዜ ድርጅቱ ሲፈቅድ ይችላል፡፡ 

ሐ. የቁጠባ ብድር ኮሚቴ አባላት ከሥራው ጋር ተያያዥነት ባለው መንገድ ከፋብሪካው ውጭ ለስብሰባ ሲጠሩ ማስረጃ ሲቀርብ የሚከፈልበት ፍቃድ ይሰጣል፡፡ 

62.4. ለፋብሪካው ሠራተኞች በፋብሪካው አድራሻ የሚመጡ ደብዳቤዎች በፋብሪካው መዝገብ ቤት ተመዝግበው ለሠራተኛ እንዲደርሱ ፋብሪካው ያደርጋል፡፡ 

62.5. ድርጅቱ ለማህበሩ መገልገያ የሚሆን ጽ/ቤት እንዲኖረው ያደርጋል፡፡ 

62.6. ድርጅቱና ማህበሩ የበዓል ዋዜማና ማግስት የፋብሪካው ሥራ ተቋርጦ ከዋዜማው በፊት ወይም በኋላ በማካካሻ እንዲሰራ በማስማማት በሚያሳልፉት ውሳኔ መሠረት የፋብሪካው ሥራ ስምምነት ላይ በተደረሰበት ቀን እንዲካካስ ማድረግ ይቻላል፡፡ 

አንቀጽ 63 

ፕሮቪደንት ፈንድ 

63.1. የፕሮቪደንት ፈንድ ማጠራቀሚያ ለእያንዳንዱ ሠራተኛ በስሙ የተለየ አካውንት ድርጅቱ ውል ከመሠረተበት ባንክ ውስጥ ይከፍታል፡፡ 

63.2. የፕሮቪደንት ፈንድ ከሠራተኛው ደመወዙን 7 በየወሩ በመቁረጥ ከድርጅቱ 11 የሚያክል በመቁረጥ በድምሩ 18 በየወሩ በተከፈተው የየአንዳንዱ ሠራተኛ አካውንት እንዲጠራቀም ያደርጋል፡፡ ሆኖም የመንግስት የጡረታ ህግ ክፍያ በአዋጅ ሲሻሻል ከሠራተኛውና ከአሰሪው ለጡረታ በሚሰበሰበው መጠን የፕሮቪደንት ተከፋዮችመም በዚያው መጠን የሚሰበሰብ ይሆናል፡፡ 

63.3. ሠራተኛው በማንኛውም ምክንያት የሥራ ውሉ ከተቋረጠ በየወሩ ከአሠሪውና ከሠራተኛ የተጠራቀመለትን ከነባንክ ወለዱ ተሰልቶ ይከፈለዋል፡፡ 

ክፍል አስራ አምስት

ጠቅላላ ስምምነቶችንና ድንጋጌዎችን በተመለከተ 

አንቀጽ 64 

የይርጋ ጊዜ 

64.1. በዚህ ህ/ስምምነት ከተጠቀሱት በስተቀር ማናቸውም የይርጋ ጥያቄ በአዋጅ ቁጥር 377/96 መሠረት ይፈጸማል፡፡ 

አንቀጽ 65

የህብረት ስምምነት ስለማሻሻል


65.1. ይህን የህብረት ስምምነት ፋብሪካውና ሠራተኛ ማህበሩ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 መሠረት ለማሻሻል ይችላሉ፡፡ 

65.2. በዚህ ህ/ስምምነት የተጠቀሱትን አንቀጾች አግባብ ያላቸው በፋብሪካው ውስጥ ያሉ ደንቦች መመሪያዎች፣ ሰነዶች፣ ትዕዛዞች የዚህ ህ/ስምምነት አካል ይሆናሉ፡፡ 

65.3. አዲስ ሁኔታዎችና አዲስ አሠራር ሲያጋጥም ፋብሪካውና ማህበር በጋራ በመነጋገር የዚህ ህብረት ስምምነት አካል እና የሆኑ በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት እንዲመዘገብ 

አንቀጽ 66

የህብረት ስምምነት ኮፒ ለሠራተኛ ማህበር ስለመስጠት 

66.1. ድርጅቱና ሠራተኛ ማህበሩ ተደራድረው ስምምነት የደረሱበትንና በማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ጸድቆ የተመዘገበውን ሰነድ ድርጅቱ ለማህበሩ ሥራ አስፈጻሚ በኮፒ እንዲደርስ ያደረጋል፡፡ 

66.2. ድርጅቱና ሠራተኛ ማህበሩም ለእያንዳንዱ ሠራተኛ የህ/ስምምነቱ ቅጂ እንዲደርስ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ 

አንቀጽ 67 

የህብረት ስምምነቱ ጸንቶ የሚቆይበት ጊዜ 

67.1. ይህ የህብረት ስምምነት በዕድገት ድርና ማግ የስፌት አክስዮን ማህበር ሥራ አመራርና በእድገት ድርና ማግ የስፌት ክር አክስዮን ማህበር መሠረታዊ ሠራተኛ ማህበር መካከል ተፈርሞ በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ቤት ጸድቆ ከተመዘገበበት ወር የመጀመሪያው ቀን አንስቶ ለሶስት ዓመት የሚያገለግል ይሆናል፡፡ 

የህብረት ስምምነት ተደራዳሪ ወገኖች 

ሀ. የድርጅቱ ተወካዮች  ኃላፊነት  ፊርማ 

  1. አቶ ተስፋዩ ያይንሸት  አስተዳደር ሥራ አስኪያጅ  _______________
  2. አቶ ተስፋዩ መዋህዶ  የባለሀብት አማካሪ   _______________
  3. አቶ አዲ አናጋው  የፈትል ምርትና ጥገና ክ/ኃ  _______________


ለ. የመሠረታዊ ሠራተኛ ማህበር ተወካዮች  ኃላፊነት  ፊርማ 

  1. አቶ ለማ በላይነህ  የማህበሩ ሊቀመንበር 
  2. አቶ እሸቱ ማሞ  የማህበሩ ም/ሊቀመንበር
  3. ወ/ሮ ሰናይት የሚ  የማህበሩ የሂሳብ ሹም 


    

 




በዕድገት ድርና ማግ የስፌት ክር አክስዮን ማህበር እና በዕድገት ድርና ማግ የስፌት ክር አክስዮን ማህበር መሠረታዊ ሠራተኛ ማኅበር መካከል ለ15ኛ ጊዜ የተደረገ የሕብረት ስምምነት -

Start date: → Not specified
End date: → Not specified
Public/private sector: → 
Concluded by:
Loading...